ስለ አሰግድ ተስፋዬ ምስክርነት… አብሮት የተጫወተው አንዋር ያሲን (ትልቁ)

ልክ በዛሬው ዕለት በ2009 ህይወቱ ያለፈው አሰግድ ተስፋዬን ማስታወሳችንን ቀጥለናል። አሁን ደግሞ ከአሰግድ ጋር በኢትዮጵያ ቡና እና ብሔራዊ ቡድን ረዥም ዓመታት አብረውት ከተጫወቱት ተጫዋቾች መካከል አንዋር ያሲን (ትልቁ) ስለ ቀድሞ የቡድን ጓደኛው ያለውን ትውስታ እንዲህ አጋርቶናል።

” አሰግድ በጣም የሚገርም ተጫዋች ፣ ብዙ ነገሮቹ አስተማሪ የሆኑ እኔ አብሬያቸው ከተጫወትኳቸው ተጫዋቾች መካከል ከሜዳ ውስጥም ከሜዳ ውጭም ለብዙዎች ምሳሌ መሆን የሚችል ተጫዋቾች ነው። በብሔራዊ ቡድንም፤ በክለብም አብሮ ለመጫወት ብዙ አጋጣሚዎች አግኝቻለው። በተጫዋችነት ዘመኔ እርሱ እንዳለው አቅም ብዙ መናገር ብችልም በተለይ የአንበልነትን ተግባርን በትክክል ያየሁበት ተጫዋች ቢኖር አሰግድ ነው። የአንበልነት ሚና ምልክት ማድረግ ብቻ ሳይሆን ከአሰልጣኝ በታች በመሆን ክለብ ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮች የመፍታት አቅም አለው። አንድ ቦታ ላይ የተፈጠሩ ችግሮችን ወድያውኑ ወደ መልካም ይቀይራቸዋል። ለምሳሌ አንድ ነገር ላጫውትህ ከትራንስ ጋር ለመጫወት ወደ መቐለ ስንሄድ መጀመርያ በአውሮፕላን ነው የሄድነው ስንመለስ በመኪና ነበር። ይገርምሀል ወደ አዲስ አበባ እየተመለስን የመኪናው ጎማ ይፈነዳል፤ ሹፌሩ ተለዋጭ ጎማ ለመቀየር ሲፈልጉ ቅያሪው ጎማ ራሱ ፈንድቶ ነበር። አስበው ረዥም ሰዓት እዛው ልንቆይ ነው። ተጫዋቾቹ ብስጭት በማለት ማጉረምረም ጀመሩ፤ ያው ታቃለህ የተጫዋች ባህርይ አስቸጋሪ ነው። በዚህ ሰዓት አሰግድ ምን ችግር አለ አንዴ ሆኗል ብሎ ሹፌሩን በሌላ መኪና ጎማ እንዲያመጡ ልኮ ተጫዋቾቹን ትጥቅ አስቀይሮ መሐል ባልገባ እንዲጫወቱ ሌላ የሚያዝናና አስቂኝ ነገር አድርገን የነበረውን ማጉረምረም እና ችግር አስረስቶ ምንም ነገር እንዳልተፈጠ አድረጎ በሠላም ወደ አዲስ አበባ የተመለስንበት ሁኔታ የማይረሳ ነው። እንዲሁም በዚህ ጉዞ ሌላ የማደንቅት ምንድነው፤ በዚህ ጨዋታ ላይ ትራንስን 5–2 አሸነፍን ነበር። ታዲያ አንድ የአየር ኃይል ትልቅ ባለስልጣን ጨዋታውን ተከታትለው ነበር። እንዳጋጣሚ እኔ ሦስት ጎል አግብቻለው። አሰግድ እና አሊ ረዲ ጥሩ ነበሩ። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ሰውዬው እነዚህን ሦስት ልጆች ጥሩልኝ ከእኔ ጋር ነው በአውሮፕላን ይዣቸው የምሄደው ይላሉ። በእንቅስቃሴያችን ተደስተው። ይገርምሀል አሰግድ አንበል ስለሆነ ሌሎቹ ተጫዋቾች በመኪና እየሄዱ እኔ በአውሮፕላን ጥዬ አልሄድም ብሎ የአውሮፕላን ግብዣውን ሳይቀበል ከቡድኑ አባላት ጋር በመኪና የሄደበት ሁኔታ ምን ያህል የአንበልነት ሚናውን የሚወጣ ትልቅ ተጫዋች መሆኑን ማሳያ ነው።

“አሰግድ በጣም ብዙ ስዕብና ያለው ሰው ነው። እንደው ስለ እርሱ ከጠየከኝ አይቀር አንድ ነገር ልጨምር በጣም ውስጤን ስለተሰማው ነው። ለብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ኢትዮጵያ ሆቴል ቁጭ ብለን ሻይ ለምን አንጠጣም ብለን ስንወጣ የብሔራዊ ቡድን ቱታ ለብሰን ነበር። ይሄን ለብሰን ‘ኧረ አይደብርም እንዴ፤ እንቀይር።’ እያለን ስናወራ ‘ምንድነው የሚደብረው ልታወቅ አይደለ የምፈልገው፤ ይህ እኮ መታወቅያዬ ክብሬ ነው።’ ያለበት አጋጣሚ ሳስታውሰው ይገርመኛል። አስበው እኛ የተረዳንበት መንገድ እና እርሱ የተረዳበት መንገድ ይለያያል። ይሄን ቱታ መልበስ ክብር እንጂ ሌላ አይደለም በማለት ያየበት መንገድ በጣም አስገርሞኝ ነበር።
” አሰግድ በጣም ቀና አስተሳሰብ ያለው ስትቀርበው ብዙ ነገሮች ያሉት አንዳንዴም እንደ ጋዜጠኛ ነበር። ለጨዋታ ወደ ተለያዩ ክልሎች ጉዞ ስናደርግ እንዳለ ሪፖርት ይፅፋል። በዚህ ሰአት ተነሳን እዚህ ጋር እንዲህ ገጠመን በአጠቃላይ በጉዞዎቹ ላይ የሚያጋጥሙ ነገሮችን ሁሉ ይፅፋል። እኔ በግሌ ብዙ ነገሮቹን ነበር የምወድለት፤ በአጋጣሚ እርሱም ይወደኛል እድለኛ ነኝ።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ