በቀጣይ ዓመት በሊጋችን የውጭ ሀገር ግብጠባቂዎች ላንመለከት ይሆን ?

ከ2013 የውድድር ዘመን አንስቶ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ግብጠባቂዎች በሊጋችን በሚካሄዱ ጨዋታዎች ላይ ላንመለከት ይሆን?

በተለያዩ ጊዜያት የሀገር ውስጥ ግብጠባቂዎች ብቃት መውረድ እና በስፋት የተሰላፊነት ዕድል ማጣት የራሳቸው ጥረት ማነስ እንዳለ ሆኖ የውጭ ግብጠባቂዎች በሊጋችን መበርከት አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን የዘርፉ ባለሙያዎች ሲናገሩ እና የሀገራችን ግብ ጠባቂዎችም በቅሬታ መልክ ሲያነሱ በተደጋጋሚ ይደመጣል። ለዚህ ምላሽ ለመስጠት ያሰበው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለሁሉም ክለቦች የዝውውር መመርያ ውሳኔ ልኳል።

በመመርያው መሠረት ከ2013 ጀምሮ በሁሉም የሊግ ውድድሮች የውጭ ሀገር ግብጠባቂዎች እንዳይጠቀሙ (እንዳያስፈርሙ) የሚል ደብዳቤ በተለያዩ የመገናኛ መንገዶች ለክለቦች መላኩን አረጋግጠናል። በዚህ ውሳኔ ዙርያ በቀጣይ ክለቦቹ እስከ ነሐሴ ሰባት ቀን ድረስ የሚሰጡት ምላሽ የሚጠበቅ ይሆናል።

ይህ ውሳኔ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ የሀገር ውስጥ ግብጠባቂዎች ድርቅ ለተመታው ሊጋችን እና ለተስፈኛ ግብጠባቂዎች መልካም ዜና ነው።

በተሰረዘው የ2012 የውድድር ዓመት ከ16 የፕሪምየር ሊግ ክለቦች መካከል 12 ክለቦች የውጪ ዜጋ ግብ ጠባቂዎችን መጠቀማቸው ይታወሳል።


ማስተካከያ: በቀደመው ዘገባችን (ሊግ ኩባንባው አዲስ ውሳኔ አስተላለፈ) ከተስፋ ቡድን በሚያድጉ ተጫዋቾች ዙርያ የተሻሻለው ደንብ ላይ የተወሰኑ የአገላለፅ ግድፈቶች በመኖራቸው ማስተካከያዎችን አካተናል። በዚህም መሠረት 5 ተጫዋቾች እንደከዚህ ቀደሙ ሙሉ ለሙሉ ወደ ዋና ቡድን የሚያድጉ ሲሆን (ከ25 ተጫዋቾች መካከል ይሆናሉ) በአዲሱ ደንብ እነዚህ የሚያድጉ ተጫዋቾች ቢያንስ በቡድኑ 50 % ጨዋታዎች ላይ እንዲሳተፉ ግዴታ ተጥሏል። ሊጉ የውሳኔውን ተፈፃሚነት ከዳኞች በሚመጣ ሪፖርት መሠረት እንደሚቆጣጠርም ተገልጿል።

ከ25 ተጫዋቾች በተጨማሪ ከዚህ ቀደም 5 የነበረው በቢጫ ቴሴራ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ቁጥር ወደ 10 ከፍ ብሏል። ይህም ከ20 ዓመት በታች ቡድን የሚጫወቱ 10 ተጫዋቾች በተመላላሽነት መጫወት ያስችላቸዋል ማለት ነው።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ