ሀዲያ ሆሳዕና ሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን አስፈረመ

ሀዲያ ሆሳዕና የቀድሞ የአዳማ ከተማ ተጫዋቾችን ማሰባሰቡን በመቀጠል አጥቂው ዳዋ ሆቴሳ እና ግብ ጠባቂው ደረጄ ዓለሙን ለማስፈረም ተስማምቷል፡፡

በናሽናል ሲሚንት እና ኦሊምፒክ ቡድን ባደረገው እንቅስቃሴ የብዙዎች ዕይታ ውስጥ የገባው ፈጣኑ አጥቂ ዳዋ ሆቴሳ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ በማምራት ሁለት የውድድር ዘመናትን ያሳለፈ ሲሆን በመቀጠል በአዳማ ከተማ ጥሩ ቆይታን ማድረግ ችሏል። የአዳማ ቆይታው በመጠናቀቁም የተነሳ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ እና በርካታ የቡድን ጓደኞቹን ተከትሎ ወደ ነብሮቹ ቤት አምርቷል፡፡

ሌላው የሀዲያ ሆሳዕና ፈራሚ ግብ ጠባቂው ደረጄ ዓለሙ ነው። የቀድሞው የሰበታ ከተማ፣ ዳሽን ቢራ፣ አአ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ግብ ጠባቂ የተሰረዘው የውድድር ዓመትን በአዳማ ከተማ ያሳለፈ ሲሆን ጃኮ ፔንዜ ባልተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ቡድኑን ሲያገለግል ቆይቷል።

ሀዲያ ሆሳዕና እስካሁን ለማስፈረም የተስማማቸው ተጫዋቾች ቁጥር አስር ደርሷል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ