የዘመናችን ከዋክብት ገፅ | ቆይታ ከፍፁም ገብረማርያም ጋር…

ፈጣኑን አጥቂ ፍፁም ገብረማርያም በዛሬው የዘመናችን ከዋክብት ገፅ ላይ እንግዳ አድርገነው አዝናኝ ጥያቄዎችን አቅርበንለታል።

በመዲናችን አዲስ አበባ ኦሎምፒያ አካባቢ ተወልዶ ያደገው ፍፁም እንደ አብዛኞቹ የሃገራችን ተጫዋቾች በአካዳሚ እና ፕሮጀክት ሳይታቀፍ ነበር የእግርኳስ ህይወቱን የጀመረው። ይልቁንም በሠፈር እና በትምህርት ቤት ውድድሮች ላይ እየተሳተፈ ራሱን እንዳጎለበተ ይናገራል። በተለይ ተወልዶ ያደገበት አካባቢ ለአዲስ አበባ ስታዲየም ቅርብ ስለነበረ እና በሠፈሩ ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾችን ያወጣው ሜዳ (35 ሜዳ) ስለነበረ በእግርኳሱ ፍቅር ለመለከፍ ጊዜ አልፈጀበትም። ከምንም በላይ ደግሞ ወንድሙ ለገሠ እግርኳስ ተጫዋች ስለነበረ እና የእርሱን ትጥቅ ለመያዝ ወደ ሜዳዎች ሲያመራ በኳሱ ዓለም ተስቦ ቀርቷል።

በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከዛም በዩኒቨርስቲ ደረጃ በሚዘጋጁ ውድድሮች ላይ የቀለም ትምህርቱን እየገፋ ውድድሮች ላይ ሲሳተፍ የነበረው ተጫዋቹ በነቀምት ዩኒቨርሲቲ እያለ የእግርኳስ ህይወቱን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግር ዕድል ትምህርቱን ከሚማርበት ከተማ ክለብ አገኘ። በዚህም በጊዜው በኦሮሚያ ሊግ ሲሳተፍ የነበረውን ነቀምት ከተማን በመቀላቀል ቡድኑ በሜዳው ብቻ ሲጫወት ግልጋሎት መስጠት ጀመረ። ከሜዳው ውጪ ሄዶ እንዳይጫወት የሆነውም ትምህርቱን ለማቋረጥ ስላልፈለገ እንደሆነ ያወሳል።

ትምህርቱን እየተማረ የዩንቨርስቲዎች ውድድሮች ላይ ነቀምት ዩንቨርስቲን ወክሎ እንዲሁም የኦሮሚያ ሊግ ውድድር ላይ ደግሞ ነቀምት ከተማን ወክሎ መጫወት የቀጠለው ፍፁም የቀለም ትምህርቱን ካገባደደ በኋላ ወደ ሙገር ሲሚንቶ አመራ። በሙገር ቤትም ሁለት ጥሩ ዓመታትን ካሳለፈ በኋላ በቅዱስ ጊዮርጊስ ታድኖ ወደ ትውልድ ከተማው አዲስ አበባ መጣ። ተጫዋቹ በፈረሰኞቹ ቤት በቆየባቸው ሁለት ዓመታት ሁለት የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ጨምሮ የጥሎ ማለፍ እና የሲቲ ካፕ ዋንጫን በማግኘት በአጭር ጊዜ ስኬትን ማጣጣም ጀመረ። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከወጣ በኋላም ወደ መብራት ኃይል፣ ወልዲያ ከተማ እና መከላከያ አምርቶ የእግርኳስ ህይወቱን ቀጥሏል። ዓምና ደግሞ አዲሱን የፕሪምየር ሊጉን ክለብ ሰበታ ከተማን ተቀላቅሎ በሊጉ መጫወት ይዟል።

ለመጀመሪያ ጊዜ በአሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው (ኢንስትራክተር) ታሪካዊ ቡድን ውስጥ ተካቶ የብሔራዊ ቡድን ህይወቱን የጀመረው ፍፁም ከዛ ጊዜ ጀምሮ መንበሩን በያዙት የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኞች ጥሪ እየቀረበለት ሃገሩን አገልግሏል። በፍጥነቱ እና ጎል ላይ ርህራሄ ቢስ በመሆኑ የሚታወቀው ይህ አጥቂ ዛሬ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ጥሩ ቆይታ አድርጓል።

የእግርኳስ አርዓያህ ማነው?

የእኔ አርዓያዎች ብዙ ናቸው። ግን በዋናነት ለገሠ የተባለ ታላቅ ወንድሜን እንደ አርዓያ እመለከትኩ ነው ያደኩት። ለገሠ በጣም ጎበዝ ተጫዋች ነበር። በክለብ ደረጃ ሳይያዝ ሙያ ቀየረ እንጂ ሠፈር ውስጥ ሲጫወት ጀግና ነበር። ከወንድሜ በተጨማሪ ዳዊት መብራቱ ለእኔ ጀግናዬ ነው። ዳዊትን በጣም ነው የማደንቀው። ከማድነቅ ጎን ለጎን እንደ አርዓያዬ አየዋለሁ። ከውጪ ደግሞ በትልቁ ሮናልዶ እና ሆንሪ እሳብ ነበር።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በኮቪድ-19 ምክንያት ከተቋረጠ በኋላ ፍፁም ጊዜውን በምን እያሳለፈ ነው?

ሊጉ ከተቋረጠ 7 ወር እየሆነው ነው። ይህ ደግሞ ለእግርኳስ ተጫዋች በጣም አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም እንደዚህ የረዘመ የእረፍት ጊዜ አሳልፈን ስለማናቅ። የሆነው ሆኖ እኔ ልምምድ እየሰራሁ፣ መጽሐፍ እያነበብኩ፣ አትክልቶችን በመንከባከብ እንዲሁም የቤተሰብ ስራዎችን በማከናወን ነው ጊዜዬን እያሳለፍኩ የምገኘው።

ኮሮና ከመጣ በኋላ አዲስ እየለመድክ ያለኸው ልማድ አለ?

አለ። የሚገርምህ በፊት ማህበራዊ ህይወቴ በጣም ደካማ ነበር። እርግጥ ውድድር ለማከናወን በየጊዜው ስለምንወጣም ሊሆን ይችላል። ግን ከሰው ጋር የነበረኝ ትስስር የቀነሰ ነበር። አሁን ላይ ግን አካባቢዬ ካለው ሰው ጋር በደንብ እየተግባባሁ ማህበራዊ ህይወቴን እያጠነከርኩ ነው። በተጨማሪም ኳስ ካቆምን በኋላ የምንሰራውን ነገር ካሁኑ ለማዘገጃጀት የስራ መንፈሱን እየተለማመድኩ ነው።

ኮሮና ጠፋ ሲባል መጀመሪያ የምታደርገው ነገር ምንድን ነው?

ሰላምታ ነው የናፈቀኝ። ወዲያው ሰው ነው የማቅፈው። እንደውም ያገኘሁትን ሰው ከጀርባ እየሄድኩ ነው የማቅፈው።

በግልህ ጥሩ ጊዜ ያሳለፍክበት ዓመት መቼ ነው?

በአንፃራዊነት ጥሩ ጊዜ እንዳሳለፍኩ የሚሰማኝ በ2003 ሙገር ቤት ነው። ገና ከዩኒቨርስቲ እንደወጣሁም ስለሆነ ሙገር የገባሁት ለእኔ ልዩ ዓመት ነበር። በሙገር ፕሪምየር ሊጉንም ሳላቅ ገና በመጀመሪያ ዓመቴ 14 ግቦችን አስቆጥሬያለሁ። ይህ ደግሞ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው። ከሙገር በተጨማሪ ጊዮርጊስ ገብቼ 2 የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ያገኘሁበትን እና አህጉራዊ ውድድሮች ላይ የተሳተፍኩባቸው ዓመታት ለእኔ ድንቅ ናቸው።

ፍፁም እግርኳስ ተጫዋች ባይሆን በምን ሙያ እናገኘው ነበር?

እግርኳስ ተጫዋች ባልሆን ነጋዴ የምሆን ይመስለኛል። ቤተሰቦቼም በንግዱ ዓለም ውስጥ ስላሉ እኔም እነሱን የምከተል ይመስለኛል። ከምንም በላይ ደግሞ የተማርኩትም ትምህርት ማርኬቲንግ እና ሴልስ ማኔጅመንት ስለሆነ በቀጥታ ንግዱን እቀላቀል ነበር። የተዋጣለት ነጋዴ ባልሆንም እንኳን አንድ እቃ በልመና ሸጬ እገባ ይሆናል(እየሳቀ)።

አብሬው ተጣምሬ መጫወት እፈልጋለሁ የምትለው ተጫዋች ማነው?

ወልዲያ 3 ወራት ብቻ የተጫወትኩት። በእነዚህ አጭር ጊዜያት ግን ሰለሞን ገብረመድህን የሚባል ምርጥ ተጫዋች ተመችቶኝ ነበር። በእግርኳስ ህይወቴ ከብዙ ተጫዋቾች ጋር ተጫውቻለሁ እሱ ግን በጣም ልዩ ችሎታ አለው። ለአጥቂ የሚመችም ተጫዋች ነው። እና ከእርሱ ጋር ብዙ ጨዋታዎችን ተጣምረን ብንጫወት ደስ ይለኛል።

እሺ አንተ አጥቂ ነህ። በተቃራኒ ስትገጥመው የሚከብድህ ተከላካይ ይኖር ይሆን?

ደጉ ደበበ ጎበዝ ነው። ጨዋታን የማንበብ አቅምም ስላለው አጨዋወቴን አጥንቶ ይይዘኛል።

በዚህ ሰዓት ከሚገኙ የሃገራችን ተጫዋቾች ያንተ ምርጥ ተጫዋች ማነው?

በጣም ምርጥ ምርጥ ተጫዋቾች አሉ። ግን ሁለቱን እንድመርጥ ይፈቀድልኝ። አንደኛው በፋሲል ከነማ የሚገኘው ሱራፌል ዳኛቸው ነው። ሁለተኛው ደግሞ በቅዱስ ጊዮርጊስ የሚገኘው አቤል ያለው ነው።

ከአሰልጣኞችስ?

ከአሰልጣኞችም ሁለት ልምረጥ። እነሱም ውበቱ አባተ እና ገብረመድህን ኃይሌ ናቸው። በሊጉ ላይ ከሚመጡ ዜጋ አሰልጣኞች ውጪ ሁለቱ ብቃታቸውን ለብዙዎች አሳይተው ማሳመን የቻሉ ናቸው። ስለዚህ እኔም ሁለቱን እመርጠለሁ። ቀድሞ ሙገር ሲያሰለጥነኝ የነበረውም ግርማ ሃብተማርያም በተጨማሪነት ለእኔ ምርጥ አሠልጣኝ ነው።

ቅፅል ስም አለህ?

የፀና ቅፅል ስም የለኝም። ግን ሙገር እያለሁ ኩኩሻ እባል ነበር። በተጨማሪም ሳጥን ውስጥ ካለኝ ነገር በመነሳት ቺቻሪቶም ይሉኝ ነበር። ግን የዘለቀ እና የፀና ቅፅል ስም አሁን ላይ የለኝም።

በእግርኳስ በጣም የተደሰትክበትን አጋጣሚ አጋራኝ?

ብሔራዊ ቡድናችን ከ31 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ሲያልፍ በጣም ነበር የተደሰትኩት። በተለይ ደግሞ እኔም የስብስቡ አካል ስለነበርኩ ልዩ ደስታ ነበር የተሰማኝ። ከዚህ ውጪ አህጉራዊ ውድድሮች ላይ ተሳትፌ ጎል ማግባት እፈልግ ነበር። በዚህም ጊዮርጊስ እያለሁ በአህጉራዊ ውድድር ወደ ማሊ ተጉዘን ስታደ ማሊየን ላይ ግብ ያስቆጠርኩበት ጨዋታ ልዩ ስሜት ይሰጠኛል።

ከየትኛው የሊጉ ክለብ ጋር ስትጋጠም ነው ደስታ የሚሰማህ?

ሙገርም ሆነ ጊዮርጊስ ሆኜ በጣም የምጠብቀው የሊጉ መርሐ-ግብር ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የሚደረገውን ጨዋታ ነው። ቡና ትልቅ ክለብ ነው። በተለይ የስታዲየሙ ድባብ ስለሚስበኝ ከቡና ጋር የምንጫወትበትን ቀን በጉጉት እጠብቃለሁ።

በእግርኳሱ ውስጥ ከሚገኙ ግለሰቦች የቅርብ ጓደኛህ ማነው?

እውነት ለመናገር ብዙ ጓደኞች ናቸው ያሉኝ። ነገርግን በይበልጥ ከዳዊት እስጢፋኖስ ጋር እቀራረባለሁ። ከዳዊት ጋር የተቀራረብነውም የትውልድ ሠፈራችንም ቅርብ ለቅርብ ስለነበረ፣ ትምህርት ቤት አንድ ላይ ስለተማርን እና ከዛም ሦስት ክለብ አብረን ስለተጫወትን ይመስለኛል።

እግርኳስ ካቆምክ በኋላ ምን ለመሆን ታስባለክ?

ወደ ስልጠናው ዓለም እንደምገባ አስባለሁ። በተለይ የእግርኳስ አካዳሚ እንዲኖረኝ እሻለሁ። እኔ አጥቂ ስለሆንኩ አካዳሚው አጥቂዎች ላይ ብቻ የሚሰራ እንዲሆን እፈልጋለሁ። ምክንያቱም ረጅሙን የእግርኳስ ህይወቴን በአጥቂ ስፍራ ስላሳለፍኩ በእነዛ ዓመታት የተማርኳቸውን ነገሮች ለታዳጊዎች ማካፈል እፈልጋለሁ። ከዚህ ጎን ለጎን ግን የንግዱን ዓለም ተቀላቅዬ መስራት እፈልጋለሁ።

የግል ህይወትህ ምን ይመስላል?

አሁን ላይ ባለትዳር ነኝ። ከባለቤቴ ጋር ከተጋባን አራት ዓመታችን ነው። ለስራ ውጪ ሄዳ ስለነበረ አራቱንም ዓመት አብረን አልኖርንም። ግን ከውጪ መጥታ አብረን መኖር ከጀመርን አሁን ላይ አንድ ዓመት ሆኖናል። እርግጥ ውድድሮች ሲቋረጡ እሷ ጋር እሄድ ነበር። አሁን ግን አብረን እየኖርን ነው።

ከባለቤትህ ጋር የተገናኛችሁበት አጋጣሚ ለየት ያለ እንደሆነ አቃለሁ። እስቲ ስለዚህ ጉዳይ አጫውተኝ?

ከባለቤቴ ጋር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለን ነው የተገናኘነው። እሷ በጣም ጎበዝ ተማሪ ነች። እና እሷ ለማንበብ እኔ ደግሞ የመፅሐፍቶችን አደራደር ለማየት ቤተ-መጽሐፍት (ላይብረሪ) ስገባ ነው ዐይኔ ያረፈባት። ከዛ ቅፅበት በኋላ እየተቀራረብን መጥተን ለትዳር በቃን። በአጠቃላይ ግን በትምህርት ቤት የተጠነሰሰው ፍቅር ነው እዚህ የደረሰው።

ፍፁም ምን የተለየ ባህሪ አለው?

የተለየ ባህሪ እንኳን የለኝም። ግን ተጫዋች ነኝ። ከዚህ በተጨማሪ የተጎዱ እና ችግረኛ ሰዎችን ከጓደኞቼ ጋር ተባብሬ መርዳት ያስደስተኛል።

🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻🌼🌻

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!