ድሬዳዋ ከተማ ሁለት ረዳት አሰልጣኞች ሾመ

ብርቱካናማዎቹ የቀድሞው ተጫዋቻቸው እና የቴክኒክ ኮሚቴ አባላቸውን የአሰልጣኝ ፍሰሀ ጡዑመልሳን ረዳቶች በማድረግ ሾሟቸዋል፡፡

ለ2013 የውድድር ዘመን ቀደም ብለው የዝውውር መስኮቱ ከመከፈቱ በፊት አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማስፈረም ሲስማሙ የሰነበቱት ድሬዳዋ ከተማዎች አሁን ደግሞ የክለቡን የአሰልጣኝ ቡድን አባላትን በደንብ ለማጠናከር በማሰብ ሁለት ረዳት አሰልጣኞች በአዲስ መልክ ሾሟል፡፡ክለቡ በተሰረዘው 2012 የውድድር አመት መጋቢት ወር ላይ ኮቪድ 19 ከመግባቱ በፊት ፉአድ የሱፍ እና እዮብ ተዋበ የተባሉ ሁለት ረዳቶች ሾሞ የነበረ ቢሆንም ሁለቱን አሰልጣኞች በማንሳት በምትኩ ኤፍሬም ጌታሁን እና ቶፊቅ እንድሪስን በቦታው ተክቷል፡፡

ኤፍሬም ጌታሁን ድሬዳዋ ከተማን በ2000 ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ፕሪምየር ሊጉ በማስገባቱ ረገድ በአማካይ ሥፍራ ላይ በመጫወት በክለቡ አይረሴ ጊዜን ያሳለፈ ሲሆን በ2004 እግርኳስን እስካቆመበት ጊዜ ድረስ የብርቱካናማዎቹን መለያ ለብሶ አገልግሏል፡፡ እግር ኳስን ካቆመ በኃለ ከ2005 ጀምሮ በግሉ ታዳጊዎች እና ሴቶችን ሰብስቦ ሲያሰለጥን የቆየ ሲሆን የክለቡን የቀደመ ባህል ስለሚያውቅ ወደ አሰልጣኝ ቡድን አባላት ቢገባ የተሻለ ነው በሚል የአሰልጣኝ ፍሰሀ ረዳት ሆኖ ተሹሟል፡፡

ሌላኛው ረዳት አሰልጣኝ በመሆን የተሾመው ቶፊቅ እንድሪስ ነው፡፡ በድሬዳዋ ከተማ ውስጥ በሚካሄደው የከፍተኛ ዲቪዚዮን ውድድር አሊ ሀብቴ ጋራዥ እና ኮተን የተባሉ ቡድኖችን አሰልጥኖ ያለፈ ሲሆን በተለይ 2009 በቀድሞው አንጋፋ ክለብ ኮተን ስያሜ የተመሠረተውን ቡድን ወልዲያ ላይ በነበረው የክልል ክለቦች ሻምፒዮና ወደ አንደኛ ሊግ እንዲያልፍ ጉልህ ድርሻ ነበራቸው። ከዛም በመቀጠል ጅቡቲ በሚገኙ የተለያዩ ክለቦች በአሰልጣኝነት የሰሩ ሲሆን በርካታ ተጫዋቾች ወደ ሀገሪቱም ሄደው እንዲጫወቱ በማመቻቸቱም ይታወቃሉ፡፡ ናሽናል ሲሜንትን በረዳት አሰልጣኝነት ለተወሰነ ጊዜ በዋና አሰልጣኝነት ያገለገሉት ቶፊቅ በድሬዳዋ ከተማ በቴክኒክ ኮሚቴ አባልነት በመስራት አሳልፈው የድሬዳዋ ከተማ ሦስተኛ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን ተሹመዋል፡፡

ድሬዳዋ ከተማ ከሁለቱ አሰልጣኞች ቀደም ብሎ ዋና አሰልጣኙ ፍሰሀ ጡዑመልሳን እና የግብ ጠባቂ አሰልጣኙ አምባዬ በፍቃዱ መኖራቸው የሚታወስ ሲሆን የአሰልጣኝ ቡድኑ ቁጥር ወደ አራት ከፍ ብሏል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!