በኢትዮጵያ ምድብ የምትገኘው ማዳጋስካር ዝግጅቷን አውሮፓ ላይ ታደርጋለች

በደቡብ ምስራቅ አፍሪካ የምትገኘው ማዳጋስካር ለአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች የምታደርገውን ዝግጅት የት እንደምታከናውን አስታውቃለች።

ለ2021 የአፍሪካ ዋንጫ (ወደ 2022 ተዘዋውሯል) ለማለፍ ዋሊያዎቹ በሚገኙበት ምድብ 11 ላይ ተደልድለው ጨዋታዎቸን እያደረጉ የሚገኙት ማዳጋስካሮች የምድቡ 3ኛ እና 4ኛ ጨዋታቸውን ከሚያደርጉበት መርሐ-ግብር በፊት የዝግጅት ጊዜያቸውን ወደ ፖርቱጋል በማቅናት ለመከወን አስበው ነበር። በፖርቱጋል በሚኖራቸው ቆይታም ከቡርኪና ፋሶ አቻቸው ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ለመከወን አልመው ነበር። ነገርግን በአውሮፓ ባለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭት ምክንያት የወዳጅነት ጨዋታውን ሞሮኮ ላይ ለመከወን ተለዋጭ ቀጠሮ አስቀመጡ። ይሁን እና ሞሮኮም የበዛ የኮቪድ ስርጭት ከሚገኝባቸው የአፍሪካ ሃገሮች መካከል አንዷ በመሆኗ ከቡርኪናፋሶ ጋር ሊደረግ የነበረውን የአቋም መለኪያ ጨዋታ ሙሉ በሙሉ ሰርዘዋል።

በርካታ በፈረንሳይ ሊግ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ያላቸው ማዳጋስካሮች ወደ ፖርቱጋል እና ሞሮኮ የሚያደርጉትን ጉዞ ከገቱ በኋላ ዝግጅታቸውን በሉክሰምበርግ እንደሚያደርጉ ተጠቁሟል። ይህም የሆነው በብሔራዊ ቡድኑ በርካታ በፈረንሳይ ሊግ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ስላሉት እና ተጫዋቾቹን ከፈረንሳይ አርቆ በመውሰድ የኮቪድ ስጋት ላይ ላለመጣል እንደሆነ ተነግሯል።

ማዳጋስካር ከኮትዲቯሩ ጨዋታ በፊት በሉክሰምበርግ በምታደርገው ዝግጅትም በሃገሪቱ ሦስተኛ ዲቪዚየን ላይ ከሚወዳደረው ስዊፍት ከተባለ ክለብ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ቀጠሮ መያዟ ተሰምቷል።

የማዳጋስካር ብሔራዊ ቡድን በምድቡ ከተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ሁለቱንም (ኢትዮጵያን 1-0 እንዲሁም ኒጀርን 6-2) አሸንፋ 6 ነጥብ ይዛ ምድቡን እየመራች እንደምትገኝ ይታወቃል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!