ሶከር መጻሕፍት |  “ፋንታሲስቲ”ዎች

ላለፉት ሳምንታት በሶከር መጻሕፍት መሰናዷችን እያቀረብንላችሁ ከሚገኘው እ.ኤ.አ. በ2006 ለህትመት ከበቃው የጆን ፉት <ካልቺዮ> የተሰኘ መጽሐፍ ላይ የተመረጠ ርዕስ ይዘን መምጣታችንን ቀጥለናል። ለዛሬም በጣልያን እግርኳስ ታሪክ ላይ ካተኮረው ከዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ ስድስት ላይ የተቀነጨበውን ሁለተኛ ክፍል እነሆ ብለናል – መልካም ንባብ!

እስከ 1980ዎቹ መጨረሻ ድረስ በጣልያንም ሆነ በዓለም እግርኳስ የመሃል ሜዳ መሪዎች እና የማጥቃት አማካዮች በሌሎች አብዶኛ የመስመር አማካዮች ወይም ተፈጥሯዊ ክህሎት በታደሉ የመሃል ሜዳ ተጫዋቾች ትልቅ እገዛ ይደረግላቸው ነበር፡፡ ኳስ እግራቸው ሥር አድርገው ወደፊት በመግፋት ችሎታቸውና የተሳኩ ቅብብሎች በመከወን ብቃታቸው የተጋጣሚ ቡድን የመከላከል አደረጃጀትን የመስበር አቅም ያላቸው እነዚህ አማካዮች ሜዳ ላይ በሚኖራቸው ሰፊ የእይታ አድማስ እንዲሁም ምናባዊ ፈጠራ ሳቢያ “ፋንታሲስቲ” የሚል መጠሪያ ወጥቶላቸዋል፡፡   

ፋንታሲስቲዎች የሜዳ ላይ ጥበበኞች ናቸው፡፡ በጨዋታ ወቅት ብዙ መሮጥ አይወዱም፤ ኳስ ለመቀበል አልያም ለመንጠቅ ጉሽሚያ ውስጥ አይገቡም፡፡ ስለዚህም ከሌሎች ተጫዋቾች እንቅስቃሴ አንጻር እነርሱ ወኔ ቢስና ሰነፍ መስለው ሊገመቱ ይችላሉ፡፡ አልፎ አልፎ በሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የሌሉ እስኪመስል ከዓይን ይሰወሩና በምትሃተኛ ብቃታቸው በቅጽበት የጨዋታን ሒደት ሲመሩ፣ ውጤት ሲቀይሩ፣ ግለት ሲያንሩ ይታያሉ፡፡ ጥሩ ብቃታቸው ላይ ሲገኙ በጨዋታው ነግስው ይወጣሉ፡፡ ከተጋጣሚያቸው ግብ ጠባቂ አናት በጥቂት ከፍታ የሚሰዷቸው የዝግታ ምቶች (chipped shots)፣ በቆሙ ኳሶች አጠቃቀም (free kicks)፣ ልኬታቸው የተመጠነ – መዳረሻቸው የማይዛነፍ አጫጭርና ረዣዥም ቅብብሎች፣ ኳሱን እግራቸው ሥር አጣብቀው ባላጋራዎቻቸውን የሚያልፉበት ዘዴ (dribble)፣ የሚያስቆጥሯቸው ግቦች፣ እይታቸው እና ሌሎችም የሜዳ ላይ ክንዋኔዎቻቸው ቅጽበታዊ ምትሃተኝነታቸውን ማሳያ ናቸው፡፡

ጣልያን የፋንታሲስቲዎች አምራች ሃገር ናት፡፡ ማሪዮ ኮሮሶ ግንባር ቀደሙ ፋንታሲስቲ ነው፡፡ የኢንተሩ ተጫዋች ታታሪ አልነበረም፤ ብዙ የመሮጥ ፍላጎትም አያሳይም፡፡ ብዙዎች ይህ የተጫዋቹ ባህርይ በተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ከፍተኛ ቁጥጥር ሥለሚደረግበት የመጣ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ኮሮሶ በተጫዋችነት ዘመኑ ወይ ገልቱ አልያም ድንቅ እንጂ መደበኛ ወይም መሃል ሆኖ አያውቅም፡፡ ለሥንፍናውም ሆነ ለልዕልናው እስከ ጽንፍ የሚያደርስ አቋም ያሳይ ነበር፡፡ ሲሮጥ የሚያዘግም ቢመስልም ከኳስ ጋር በበቂ ሁኔታ ሲፈጥን ይስተዋላል፡፡ በሃገሪቱ ታዋቂ ከሆኑት የጨዋታ ቀጥታ ስርጭት አስተላላፊዎች አንዱ የነበረው ኤድሙንዶ ቤርሴሊ ” በዚያን ጊዜ በእግርኳስ ታጋይ መሆን የመብት ወይም የፍላጎት ጉዳይ ነበር፡፡ እግርኳስ ማንም ሰው በሚችለው አቅም ሊሳተፍ የሚችልበት ጨዋታ ነበር፡፡ ስለዚህም ችሎታ ከታጋይነት በላይ ዋጋ ይሰጠዋል፡፡ እያንዳንዱ ሰው በላቀ ብቃት ኳስ መጫወት እስከቻለ ድረስ ተመራጭ መሆኑ አይቀርም፡፡ ኳስ ኮሮሶ እግር ሥር ስትደርስ የስታዲየሙ ታዳሚ በሙሉ ጸጥ-ረጭ ይላል፡፡ በእግርኳሱ ዓለም ታሪክ የኮሮሰን ዓይነት ተዓምር ያሳዩን ተጫዋቾች ጥቂት ናቸው፡፡ የዚህኛው ዘመን አጨዋወት ጥድፈት ማሪዮ ኮሮሶን መሰል ተጫዋቾች “የቅንጦት እግርኳሳኞች” ያደርጋቸዋል፡፡

ጂጂ ሜሮኒም ሌላው ተዓምረኛ ጣልያናዊ ፋንታሲስቲ ነበር፡፡ ሜሮኒ ሌሎች ተጫዋቾች ሊያደርጉ አይደለም ሊሞክሩ እንኳ የማይቻላቸውን ግቦች ያስቆጥራል፤ በረጃጅም ቅልጥሞቹ በሚሰራቸው ፊንታዎች የተጋጣሚን ተከላካዮች ያሸብራል፡፡ በወጣትነቱ በአጭሩ የተቀጨው ሜሮኒ በ1960ዎቹ በጄኖኣ የክለቡ ጣዖት ለመሆን ችሏል፡፡

የፋንታሲስቲዎችን ምንነት በሚመለከት fantasista 10.cu.uk የተባለው ድረ-ገጽ ከዚህ በታች የሚከተለውን ግሩም ጽሁፍ አቅርቧል፡፡ ፋንታሲስቲዎች አዘወትረው “10-ቁጥር” መለያ ይለብሳሉ፡፡ ጣልያኖች” 10- ምትሃተኛ ቁጥር ነው፡፡” ይላሉ፡፡ በየትኛውም የስፖርት ዘርፍ የዚህን  መለያ ያህል አያሌ ተከታዮችን ያፈራና የተወደደ አልታየም፡፡ መለያው የግኝትና የፈጠራ ምንጭ ተደርጎ ይታሰባል፡፡ ብዙውን ጊዜ ይህን መለያ እንዲለብሱ የሚፈቀድላቸው ተጫዋቾች ምናብ ከሳችና አዝናኝ ናቸው፡፡ በጨዋታ ላይ የእነርሱ ብቻ የሚመስል ምትሃታዊ ጥበብ ያሳያሉ፡፡ እነርሱ ተፈጥሯዊ የማጥቃት አማካዮች ናቸው፡፡ በራስ የማሰብ ነጻነት፣ የመንቀሳቀሻ ቦታ እና ጊዜ የሚነሳቸው ታክቲካዊ ተልዕኮ ሜዳ ላይ ምቾት እንዳይሰማቸው ያደርጋቸዋል፡፡ ባለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት በዘመናዊ እግርኳስ እየተለመደ የመጣው ሜዳ ሙሉ የማካለል ኃላፊነት ደግሞ ይበልጡን የማይወዱት ግዴታ ሆኖባቸዋል፡፡ ባለፉት አስራአምስት ዓመታት እንኳ በአሰልጣኞቻቸው የሚጣልባቸው እምነት እየቀነሰ እና የእነርሱን አስፈላጊነት አጠያያቂ የሚያደርጉ ታክቲካዊ ሚናዎች ፋንታሲስቲዎችን የቅንጦት ተጫዋቾች እንደሆኑ እንዲታሰብ አድርጓል፡፡ በዚህም ሳቢያ እነዚህ ተጫዋቾች ቀድመው ከሚታወቁበት አጨዋወት በተለየ ሌሎች ሚናዎችን እንዲላመዱ ተገደዋል፡፡ ሜዳ ላይ የነበራቸው አንጻራዊ የእንቅስቃሴያቸው መነሻ ክልልም እየተቀየረ ይገኛል፡፡ 

በእርግጥም የድሮዎቹ 10-ቁጥሮች ከዘመናዊው እግርኳስ እየጠፉ ናቸው፡፡ ታዋቂው እንግሊዛዊ የታክቲክ ጸሃፊ ጆናታን ዊልሰን በ”4-4-2 መጽሄት” ላይ ባቀረበው ጽሁፍ ” ጥንታውያኑ የማጥቃት አማካዮች ነባር የሜዳ ላይ ሚናቸውን እንዲተገብሩ መፍቀድ ከባድ እየሆነ መጥቷል፤ እናም በዚህ ሚና ክህሎቱ ያላቸው ተጫዋቾች ሌሎች ተደራቢ የሜዳ ላይ ኃላፊነቶች መወጣትን መልመድ ይጠበቅባቸዋል፡፡” ሲል ኃሳቡን አስፍሯል፡፡ ይህ ሲባል ግን ጨዋታ አቀጣጣዮቹ ተጫዋቾች ሙሉ በሙሉ ከጨዋታው ተገልለዋል ማለት እንዳልሆነ ሊታሰብ ይገባል፡፡ በሌላ ሚና እና የመጫወቻ ስፍራ እነዚሁ ተጫዋቾች ሲጫወቱ እንመለከታቸዋለን፡፡ ይህን ለማረጋገጥ ሊዮኔል ሜሲ፣ ሮናልዲንሆ ጋውቾ፣ አንድሬስ ኤኒየሽታ፣ ዌስሊ ሽናይደርንና የመሳሰሉትን መጥቀሱ በቂ ይሆናል፡፡ እነዚህ ታላላቅ ተጫዋቾች በሌሎች የሜዳ ላይ ሚናዎች የተሳካ እንቅስቃሴ አድርገው ከእግርኳሱ ከዋክብት ጎራ መሰለፍ ቢችሉም የመሰረታዊ ክህሎታቸው መነሻ የቀድሞዎቹ ” 10-ቁጥሮች” ወይም የፋንታሲስቲዎችን አዕምሮ የተላበሰ የአጨዋወት ሥልት መከተላቸው ነው፡፡

አንድን የአጥቂ አማካይ ከነባሮቹ ተፈጥሯዊ ፋንታሲስቲ ለመመደብ ምን አይነት መመዘኛዎችን መቃኘት ይኖርብናል? በመለያ ቁጥሩ ወይስ በሌላ? ከላይ እንደተገለጸው ቁጥሩ በእግርኳስ ምትሃታዊ ነው፡፡ መለያውም የፋንታሲስቲዎች አጨዋወት መገለጫ ሊሆን ይችላል፡፡ በአንድ ቡድን ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ተጫዋቾች ለሚለብሱት መለያ ቁጥር ሲሰጣቸው ወጥ የነበረው የመለያ ቁጥሮች አሰጣጥ ሥርዓት እየዘመነ ሄደ፡፡ ስለዚህም ተጫዋቾች ያሻቸውን የመለያ ቁጥር የመልበስ ነጻነት ሲያገኙ ፋንታሲስቲዎቹ ሌሎቹንም ቁጥሮች
ይመርጡ ጀመር፡፡ የዚነዲን ዚዳንን ሁኔታ ማንሳት ይቻላል፡፡ በጁቬንቱስ 21-ቁጥር፣ በሪያል ማድሪድ ደግሞ 5-ቁጥር መለያ ይለብስ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ለፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ሲጫወት ከ10-ቁጥር መለያ ውጪ ምርጫ አልነበረውም፡፡ ቀደምቶቹ ፋንታሲስቲዎች 10-ቁጥር መለያ ምልክታቸው ሆኖ ቆይቷል፡፡ ፋንታሲስቲዎችን በሌሎችም ጉዳዮች ከተቀሩት ተጫዋቾች እንለያቸዋለን፡፡ እነዚህ የአጥቂ አማካዮች ብርቆች ናቸው፡፡ እግርኳስ ጨዋታን ማራኪ የማድረግ ተሰጥዖ አላቸው፡፡ በፈጠራ ክህሎታቸው ምክንያት በደጋፊዎቻቸው በልዩ ዓይንና ስስት ይታያሉ፡፡ በብቃታቸው የከፍታ ጫፍ ሲገኙ በሜዳ ላይ ትንግርታዊ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ፡፡ በጨዋታ ወቅት ከባዱን ኃላፊነት በአስገራሚ ብልሃት ይወጡታል፡፡ ድሮ-ድሮ በጣት የሚቆጠሩ ቢሆኑም በየቡድኑ አንድ እንኳ ፋንታሲስቲ አይጠፉም ነበር፡፡ በእርግጥ ኮከቦቹ ፋንታሲስቲዎች ልዩ እና ጥቂት ናቸው፡፡ ታዲያ ፋንታሲስቲዎች ሁልጊዜ አይሳካላቸውም፡፡ አንዳንዴ ሜዳ ላይ ያልገቡ ያህል ከአይን ርቀው ይውላሉ፡፡

ፋንቲሲስቲዎች በሚጫወቱበት የሜዳ ክልልም
አንጻራዊ ነጻነት ይሻሉ፡፡ ብዙውን ጊዜ ከመሃለኛው ክፍል ይልቅ ከአጥቂዎች ጀርባ በመሆን ይጫወታሉ፡፡ ተጫዋቾቹ በሚሰጣቸው ሚና መሰረት መጫወቻ ቦታቸው መጠነኛ መሸጋሽጎች ተደርጎበት በሚከተሉት ሁለት ክልሎች ይወሰናል፡፡
ይኸውም፦
1) ይበልጡን የፊት መስመር ተሰላፊነት ሚና በያዘ ኃላፊነት
2) ከፊት መስመር ተሰላፊነት ይልቅ የመሃል ሜዳ አማካኝነት ያመዘነበት ሚና

በሁለቱም ሁኔታዎች የሚጫወቱትን ፋንታሲስቲዎች የሚያመሳስላቸው የጋራ ባህርይ የመከላከል ኃላፊነትን ለመወጣት የማይፈልጉ መሆናቸው ነው፡፡ እነዚህ ተጫዋቾች በተለያዩ ሃገራት የተለያዩ ስያሜዎች አሏቸው፡፡ በኢትዮጵያ ከተለመደውና ጨዋታ አቀጣጣይ ከሚሰኝ ስማቸው ውጪ <<ፔሌይ-ሜከር>>፣ <<ኢንጋንቼ>>፣ <<ፑንታ ደላንቻ>>፣ <<ሆል-ፕሌየር>>፣ <<10-ቁጥር>>፣… ያለ እነርሱ እግርኳስ አሁን የደረሰበት የመወደድ ደረጃ ላይ ሊደርስ እንደማይችል ሁሉንም ያስማማል፡፡

ይቀጥላል…

የመጽሃፉ ደራሲ ጆን ማኪንቶሽ ፉት ይባላል፡፡ እንግሊዊው ጸሃፊ የጣልያንን ጓዳ-ጎድጓዳ አብጠርጥረው ከሚያውቁ የውጭ ምሁራን መካከል ይጠቀሳል፡፡ በበርካታ የጣልያን እና እንግሊዝ ዩኒቨርሲቲዎችም የጣልያንን ታሪክ አስተምሯል፡፡ በሃገሪቱ ፖለቲካ፣ ፍልስፍና እና ምጣኔ ኃብት ዙሪያ የሚያጠነጥኑ የታሪክ መጻሕፍትም አበርክቷል፡፡ በተለያዩ ብዙኃን መገናኛዎችም ጥልቀት ያላቸው ጥናቶቹን ያቀርባል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ