ይህንን ያውቁ ኖሯል? (፫) | የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን…

ዕለተ ሀሙስ በምናቀርበው “ይህንን ያውቁ ኖሯል?” አምዳችን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን የተመለከቱ ዕውነታዎችን በሁለት ክፍል ጥንቅር ወደ እናንተ ስናደርስ ቆይተናም። ዛሬም በተከታይ ክፍል ጥንክር ብሔራዊ ቡድኑን እና የአፍሪካ ዋንጫን የተመለከቱ እውነታዎችን አዘጋጅተን ቀርበናል።

*ማስታወሻ : የተጠቀሱት ዘመናት በሙሉ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ናቸው።

– ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ዋንጫ መስራቾች አንዷ ስትሆን በመጀመርያው ውድድር ላይ ከተሳተፉት ሦስት ሀገራት መካከልም አንዷ ነበረች። የመጀመርያ ጨዋታዋ ሊሆን የነበረው ከደቡብ አፍሪካ ጋር ቢሆንም ሀገሪቷ በአፓርታይድ ምክንያት በመታገዷ በቀጥታ ወደ ፍፃሜ አልፋ ከግብፅ ጋር ተጫውታለች።

– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአጠቃላይ ለአሰር ጊዜያት በአፍሪካ ዋንጫ ላይ የተሳተፈ ሲሆን ከነዚህ መካከል ሦስቱን በአዘጋጅነት፣ አንዱን በቻምፒዮንነት እንዲሁም ሁለቱን ያለማጣርያ ወደ ውድድሩ ተቀላቅሏል። በቀሪዎቹ አራት ውድድሮች ደግሞ በማጣርያ ተቀላቅሏል።

– ኢትዮጵያ ውድድሩን አንድ ጊዜ (በ1954) በአሸናፊነት ስታጠናቅቅ አንድ ጊዜ ሁለተኛ (ያለ ጨዋታ ለፍፃሜ ደርሳ)፣ አንድ ጊዜ ሦስተኛ (ያለ ደረጃ ጨዋታ) እንዲሁም ሦስት ጊዜ ደግሞ አራተኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች። በቀሪዎቹ አምስት ውድድሮች ከምድብ ማለፍ አልቻለችም።

– ኢትዮጵያ በአጠቃላይ የውድድሩ ተሳትፎዋ 27 ጨዋታ ስታደርግ 7 አሸንፋ፣ በ3 ጨዋታ አቻ ተለያይታ 17 ጨዋታ ተሸንፋለች።

– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተጠቀሱት ጨዋታዎች 29 ጎሎችን ሲያስቆጥር 60 ጎሎች ደግሞ አስተናግዷል።

– በውድድሩ ኢትዮጵያ በአንድ ጨዋታ በርካታ ጎሎችን ያስቆጠረችው በ1954 ግብፅ እና ቱኒዚያን እንዲሁም በ1955 ቱኒዚያን 4-2 ባሸነፈችበት ግጥሚያ ነው።

– በተቃራኒው በአንድ ጨዋታ በርካታ ጎል የተቆጠረባት በ1962 ውድድር ነው። በዚህ ጊዜ በምድብ ሦስተኛ ጨዋታ አይቮሪኮስት ጋር ተገናንታ 6 ግቦችን አስተናግዳ 6-1 ተሸንፋለች።

– የኢትዮጵያን የመጀመርያ የአፍሪካ ዋንጫ ጎል ያስቆጠረው ሉቻኖ ቫሳሎ ነው። ኢትዮጵያ በ1954 ቱኒዚያን 4-2 ስታሸንፍ በስምንተኛው ደቂቃ ሉቻኖ ከፍፁም ቅጣት ምት የመጀመርያውን ጎል ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አስቆጥሯል።

– በአንፃሩ የመጨረሻውን ጎል ያስቆጠረው ተጫዋች አዳነ ግርማ ነው። በ2005 ደቡብ አፍሪካ ላይ በተደረገው ውድድር ዛምቢያ ላይ አዳነ የመጨረሻውን የብሔራዊ ቡድኑን ጎል ከመረብ አገናኝቷል።

– በአፍሪካ ዋንጫው ላይ ለኢትዮጵያ በርካታ ጎሎችን ያስቆጠረው ተጫዋች መንግሥቱ ወርቁ ናቸው። በፍፃሜ ያስቆጠሩትን አንድ ጎል ጨምሮ በአጠቃል ዘጠኝ ጎሎችን ለኢትዮጵያ በዚህ የአህጉሪቱ ትልቅ ውድድር ላይ አስቆጥረዋል። (በአንዳንድ የታሪክ መዛግብት ስምንት ጎል የሚል ተጠቅሷል)

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!