ሪፖርት | ዋልያዎቹ ዳግም በአቋም መለኪያ ጨዋታ ተረተዋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአዲስ አበባ ስታዲየም ከዛምቢያ አቻው ጋር ያደረገውን የአቋም መፈተሻ ጨዋታ 3-1 በሆነ ውጤት ተሸንፏል።

በኮቪድ-19 ምክንያት ወደ 2022 ለተሸጋገረው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የማጣሪያ ጨዋታዎች እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በህዳር ወር የመጀመሪያ ቀናት ከኒጀር ጋር ላለበት የምድቡ 3ኛ እና 4ኛ ጨዋታ ይረዳው ዘንድ በዛሬው ዕለት ሁለተኛ የአቋም መለኪያ ጨዋታውን ከዛምቢያ ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም አከናውኗል። በጨዋታውም ተጋባዦቹ ዛምቢያዎች እጅግ ከፍተኛ የጨዋታ ብልጫ በማሳየት ጨዋታውን 3-1 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።

መስከረም 18 በተሠጠ ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ የዋሊያዎቹ ዋና አሠልጣኝ በመሆን የተሾሙት አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከሀሙሱ የመጀመሪያ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ስድስት ለውጦችን አድርገው ለጨዋታው ቀርበዋል። በዚህም አሠልጣኙ አቤል ማሞ፣ ሱሌማን ሀሚድ፣ አንተነህ ተስፋዬ፣ አስቻለው ታመነ፣ ኃይለሚካኤል አደፍርስ፣ ሀብታሙ ተከስተ፣ ታፈሰ ሰለሞን፣ ሱራፌል ዳኛቸው፣ አማኑኤል ገ/ሚካኤል፣ ሙጁብ ቃሲም እና አዲስ ግደይ በቋሚነት ተጠቅመው ጨዋታውን ጀምረዋል። በጨዋታውም ተጋባዦቹ ዛምቢያዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ፍፁም የጨዋታ ብልጫ ሲይዙ ባለሜዳዎቹ ደግሞ በአንፃራዊነት በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታውን የሃይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው ታይተዋል።

ኳስን ከግብ ክልላቸው ጀምሮ መስርቶ ለመውጣት ሲጥሩ የነበሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች አብዛኞቹ ጥረቶቻቸው የተሳካ ቢመስሉም በተወሰኑ አጋጣሚዎች ግን ኳሱን በአደጋ ቀጠና እየተነጠቁ ራሳቸው ላይ አደጋን ሲጋብዙ ታይቷል። በዚህ እንቅስቃሴም በአስረኛው ደቂቃ ዛምቢያዎች ተጭነው በመጫወታቸው ያገኙትን ኳስ በጥሩ ቅንጅት ወደ ዋሊያዎቹ የግብ ክልል ይዘው በማምራት የመጀመሪያ ሙከራ አድርገዋል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላም ሀብታሙ ተከስተ በመሐል ሜዳ የግራ ክፍል ለኃይለሚካኤል አደፍርስ ሊያቀብል የነበረውን ኳስ ኮሊንስ አቋርጦ በፍጥነት ወደ ፊት ያሳለፈውን ኳስ ኢማኑኤል ቻቡላ ከሳጥን ውስጥ የአቤል ማሞን አቋቋም ተመልክቶ በቀላሉ ቀዳሚዋን ጎል ለቡድኑ አስቆጥሯል።

ከኳስ ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ በራሳቸው የሜዳ ክልል ብቻ ተገድቦ የታየው ዋልያዎቹ እስከ 19ኛው ደቂቃ ድረስ የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ማድረግ ተስኗቸው ነበር። በዚህም ደቂቃ ሙጂብ ቃሲም ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ወደ ግብነት ለመቀየር ሞክሮ ወጥቶበታል። ጨዋታውን በሚፈልጉት መንገድ ሲቆጣጠሩ የነበሩት ዛምቢያዎች በ23ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ጎል አስቆጥረው መሪነታቸውን አስፍተዋል። በዚህ ደቂቃ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ከኋላ ኳስ ለማስጀመር ባደረጉት ጥረት ሀብታሙ እና ታፈሰ ሲቀባበሉ ዛምቢያዎች ቀምተው የተሻማው ኳስ ሲመለስ ቻቡላ ወደ ግብ መቶ አቤል ሲመልሰው ያገኘውን ኳስ ሲኮምቤ በቀላሉ ወደ ግብነት ቀይሮታል። በዚህ ግብ ላይም እንደመጀመርያው ጎል ሁሉ የቅብብል ስህተት፣ ያልተደራጀ መከላከል እና የግብጠባቂ ድክመት በጉልህ ታይቷል።

ፈጣን የመስመር ላይ ሽግግሮችን (ከመከላከል ወደ ማጥቃት) ሲከተሉ የነበሩት ቺፖሎፖሎዎቹ በተለይ በቀኝ መስመር በኩል የጥቃተቀቸውን ትኩረት በማድረግ ወደ ዋሊያዎቹ የግብ ክልል መድረስ ቀጥለዋል። በ36ኛው ደቂቃም በዛምቢያ የጎል ክልል ኮንድዋኒ ቺቦኒ ከኢትዮጵያ ተጫዋቾች ያስጣለው ኳስ በሁለት ቅብብል ብቻ ወደ ኢትዮጵያ የሜዳ ክፍል ደርሶ ኢማኑኤል ቻቡላ ረጅም ርቀት ኳሱን ይዞ በመግፋት ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል መትቶ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሶስተኛ ጎል አስቆጥሯል። በዚህ ጎል ላይም ያልተናበበው የተከላካይ ክፍል ቻቡላ ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ እንዳይገኝ እና አምልጦ እንዲወጣ አድርጓል።

ፈጣኑን የዛምቢያ ጥቃት መቋቋም የተሳናቸው ኢትዮጵያዎች ሦስተኛውን ግብ ካስተናገዱ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በተገኘ የቅጣት ምት ወደ ጨዋታው በቶሎ ለመመለስ ጥረዋል። ነገርግን ከርቀት የተገኘውን የቅጣት ምት ሱራፌል ወደ ጎልነት መቀየር ሳይችል ወጥቶበታል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት አልበርት ካዋንዳ ዳግም ወደ ዋሊያው የግብ ክልል ደርሶ አራተኛ ጎል ለማስቆጠር ሞክሯል። በደቂቃ ልዩነትም አሚቲ ሻሜንዴ ያመቻቸለትን ነፃ ኳስ ከጎሉ ፊት ለፊት የነበረው ኮሊንስ ሲኮምቤ መትቶ የጎሉ አግዳሚ ለትሞ የወጣበት አጋጣሚ በመጀመርያው አጋማሽ የዛምቢያን መሪነት ወደ 4-0 ሊያሳድግ የሚችል ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ጌታነህ ከበደ፣ ጋዲሳ መብራቴ፣ ሀይደር ሸረፋ፣ ከነዓን ማርክነህ፣ አማኑኤል ዮሐንስ፣ መሳይ ፓውሎስ፣ አምሳሉ ጥላሁን፣ ሽመክት ጉግሳ እና ተክለማርያም ሻንቆን በሱሌማን፣ ኃ/ሚካኤል፣ አንተነህ፣ ሀብታሙ፣ ታፈሰ፣ ሙጂብ፣ ሱራፌል፣ አማኑኤል እና አቤል ተክቶ ወደ ሜዳ አስገብቷል። በዚህ አጋማሽም ዋሊያዎቹ በአንፃራዊነት የተሻለ የጨዋታ እንቅስቃሴ በማሳየት የግቡን ልዩነት ለማጥበብ ሲጥሩ ታይቷል። የአጋማሹን የመጀመሪያ ሙከራ ጋዲሳ በ52ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ያደረገ ሲሆን ኳስ እና መረብ ግን ሳይገናኙ ቀርተዋል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም ተቀይሮ የገባው ከነዓን ከአዲስ የተሻገረለትን ኳስ ከፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ጫፍ ላይ ሆኖ ወደ ጎል ቢመታትውም ኳስ ዒላማዋን ስታ ወታበታለች።

ጨዋታውን በመጀመሪያው አጋማሽ ያገባደዱ የሚመስለው ዛምቢያዎች በዚህኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በርካታ ለውጦቸን በማድረግ አቅማቸውን ቆጥበው ተጫውተዋል። ፍጥነቶች የታከሉበት የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎችንም ገድበው ታይተዋል። ይህ የተጋጣሚያቸው መቀዛቀዝ የጠቀማቸው ዋሊያዎቹ በበኩላቸው ባልተደራጀ መንገድ ቢሆንም በተለያዩ አማራጮች ወደ ግብ መድረሳቸውን ቀጥለዋል። በ60ኛው ደቂቃም ከርቀት የተገኘውን የቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ ወደ ግብ መትቶት ግብ ጠባቂው ጃክሰን ካኩታ በቀላሉ አምክኖበታል። ይህንን ሙከራ ያደረገው ጌታነህ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም በቀኝ መስመር ያገኘውን ኳስ ዳግም ወደ ግብነት ለመቀየር ጥሮ ኳስ የግቡን የጎን መረብ ታካ ወጥታበታች።

በመጀመሪያው አጋማሽ የጎንዮሽ እና የኋልዮሽ ኳሶችን አዘውትረው ሲጠቀሙ የነበሩት የአሠልጣኝ ውበቱ ተጫዋቾች በዚህኛው አጋማሽ በተረጋጋ መንፈስ የፊትዮሽ ኳሶችን በአንፃራዊነት በተሻለ መልኩ ለመጠቀም ሞክረዋል። በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባውን ጌታነህ ከበደን ታሳቢ ያደረጉ ተንጠልጣይ እና ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶችን ቡድኑ ሲጠቀም ተስተውሏል። ከዚህ በተጨማሪም በ8 ቁጥር ቦታ የተሰለፉት ሀይደር እና ከነዓን ከሳጥን ውጪ በመሆን በተከላካዮች ተገጭተው የሚመለሱ ኳሶችን ወደ ግብነት ለመቀየር ጥረዋል። በዚህ አጨዋወትም ከነዓን በ80ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተሻገረው ኳስ በተከላካዮች ተጨርፎ ሲመለስ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብነት ለመቀየር ሞክሮ ነበር። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም በተመሳሳይ በተከላካዮች ተገጭቶ የተመለሰውን ኳስ በሳጥን ውስጥ የነበረው ጌታነህ በጥብቅ ምት ኳሷን ወደ ጎል ቢልካትም ዒላማዋን ስታ ወደ ውጪ ወጥታበታለች።

በሁለተኛው አጋማሽ ድንቅ ብቃቱን ሲያሳይ የነበረው አምበሉ ጌታነህ ጨዋታው ሊገባደድ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ቡድኑን በባዶ ከመሸነፍ ያዳነች ኳስ ከመረብ አገናኝቷል። በዚህ ደቂቃ ሽመክት ጉግሳ በጥሩ ሁኔታ ወደፊት የጣለውን ኳስ ከነዓን ማርክነህ በአግባቡ ተቆጣጥሮ በጥሩ አቋቋም ላይ ለነበረው ጌታነህ አመቻችቶለት አምበሉ አጋጣሚውን ወደ ጎልነት ቀይሮታል። ዋሊያዎቹ በቀሩት ደቂቃዎች የግቡን ልዩነት ለማጥበብ ፍላጎት ቢያሳዩም ረጃጅሞቹም የዛምቢያ ተከላካዮች ማለፍ ተስኗቸዋል። ጨዋታውም በዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን 3-1 አሸናፊነት ተገባዷል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!