የአአ እግርኳስ ፌዴሬሽን ምርጫ የሚደረግበት ቀን ታውቋል

በበርካታ ውዝግቦች ተራዝሞ የነበረው የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈፃሚ ምርጫ የሚደረግበት ቀን ሲታወቅ በርካታ የቀድሞ አመራሮችም በተወዳዳሪነት እንደማይቀርቡ ተረጋግጧል።

የመዲናችን አዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ምርጫ ከወራት በፊት ሊደረግ ቀነ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረ ቢሆንም በበርካታ ውዝግቦች ታጅቦ መራዘሙ ይታወሳል። የምርጫ ሥነ-ስርዓቱም በአጣሪ ኮሚቴ እንዲጣራ እና በጊዜው የነበሩ ችግሮች እንዲፈቱ ከተደረገ በኋላ የተራዘመው ምርጫ በህዳር ወር አጋማሽ እንደሚከናወን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል። በዚህም ፌዴሬሽኑን በፕሬዝዳንትነት እና ሥራ አስፈፃሚነት ለመምራት አጠቃላይ 23 ግለሠቦች ከክፍለ ከተሞች፣ ክለቦች እና ማኅበራር በእጩነት የቀረቡ ቢሆንም አጣሪ ኮሚቴው ዶክመንቶችን እና መረጃዎችን በመመርመር የመጨረሻ 13 ግለሰቦቸን በእጩነት መያዙን አስታውቋል።

የወቅቱን የፌዴሬሽኑን ፕሬዝዳንት አቶ ኃይለየሱስ ፍሰሃን (ኢ/ር) ጨምሮ አቶ ገዛኸኝ ምንዳዬ እና አቶ የኔነህ በቀለ (ኢ/ር) ፌዴሬሽኑን በቀጣይ በበላይነት ለመምራት በእጩነት ስማቸው የተላከ ቢሆንም አቶ የኔነህ እጩነታቸውን በፊርማቸው ባለማረጋገጣቸው ከውድድሩ ውጪ እንደሆኑ ተነግሯል። በሥራ አስፈፃሚነት ከተያዙት 11 እጩዎች ውስጥ ደግሞ በቀደመው ምርጫ ራሳቸውን ባለቀ ሰዓት ያገለሉት አሠልጣኝ አስራት ኃይሌ መካተታቸው ተረጋግጧል።

አጣሪ ኮሚቴው እጩዎችን አጣርቶ ባወጣው የስም ዝርዝር ውስጥ ፌዴሬሽኑን ከዚህ ቀደም ሲመሩ የነበሩት አቶ በለጠ ዘውዴ ፣ አቶ ዩናስ ሀጎስ እና ወ/ሮ ሰርካለም ከበደ አለመካተታቸው አግራሞትን ፈጥሯል።


© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!