ሚካኤል ደስታ ወደ ስሑል ሽረ አምርቷል

ላለፉት ሦስት የውድድር ዓመታት መቐለ 70 እንደርታን በአምበልነት የመራው ሚካኤል ደስታ ከክለቡ ጋር ተለያይቶ ለስሑል ሽረ ፊርማውን አኑሯል።

የእግርኳስ ሕይወቱን በመቐለ ጀምሮ ወደ ጣልያን በማምራት በሃገሪቱ የታዳጊ ቡድኖች ቆይታ አድርጎ በድጋሚ ወደ መቐለ ተመልሶ በትራንስ ኢትዮጵያ የክለብ እግርኳስ የጀመረው “ጣልያኑ” ለሰባት ዓመታት በትራንስ ቆይታ ካደረገ በኋላ በ2000 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መድን አቅንቷል። በመድን ለአንድ የውድድር ዓመት ከተጫወተ በኃላም ወደ ፈረሰኞቹ አቅንቶ ለሁለት ዓመታት ቆይታ በማድረግ ወደ መከላከያ አቅንቶ ከክለቡ ጋር እስከ 2009 መጨረሻ ድረስ ተጫውቷል። 2010 ወደ አዲስ አዲጊው መቐለ 70 እንደርታ ካመራ በኃላም በአምበልነት እስከ ባለፈው ዓመት ከክለቡ ጋር ቆይታ አድርጎ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ አንስቷል።

ተጫዋቹ ከምዓም አናብስት ጋር ያቸው ውል መጠናቀቁን ተከትሎ ለስሑል ሽረ ፊርማውን ያኖረ ሲሆን በዛሬው ዕለት ከቡድኑ ጋር ልምምድ እንደጀመረ ክለቡ አስታውቋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!