መንግሥቱ ወርቁ ሲታወሱ (፲፩) | የታላቁ ሰው የባይተዋርነት ጊዜ

በህይወት የሌሉ የእግርኳስ ሰዎችን በምናስታውስበት አምዳችን የቀድሞው እና በበርካቶች ዘንድ የምን ጊዜውም ታላቅ እግርኳስ ተጫዋች እንደሆኑ የሚነገርላቸው መንግሥቱ ወርቁን እያሰብን እንገኛለን። ለዛሬ የመንግሥቱ ወርቁን የስድስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማግስት ትውስታ እናነሳለን።

ማስታወሻ ፡ በገነነ መኩሪያ በመፅሀፍ መልክ የተዘጋጀው ከመንግስቱ ወርቁ ጋር የተደረገው ቃለ ምልልስ ፣ ‘ይድረስ ለባለንብረቱ’ የሚለው በፋንታሁን ኃይሌ ፣ ኃይማኖት ቃኘው እና ተዘራ አለነ የተዘጋጀው መፅሀፍ እና በልሣነ ጊዮርጊስ ጋዜጣ መንግስቱ ወርቁ የተዘከሩባቸው ሕትመቶች ለዚህ ፅሁፍ ግብአትነት ተጠቅመናል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በስድስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ እንደታሰበው ሳይሆን ቀርቶ ለፍፃሜው እንኳን ማለፍ ሳይችል እንደቀረ ፣ ይህ የሆነበትን ዋነኛ ምክንያትም ጭምር ሳምንት እንዳስነበብናችሁ ይታወሳል። ለፍፃሜ ለማለፍ ከተደረገው እና ኢትዮጵያ በኮንጎ ብራዛቪል በጭማሪ ደቂቃ 3-2 ከተሸነፈች ጨዋታ በኋላ የነበረው ጊዜ ደግሞ ለታላቁ መንግሥቱ ወርቁ እጅግ አስከፊ ነበር። እንደ ቡድኑ አጥቂ እና ቁልፍ ተጫዋች ሽንፈቱ ሊፈጠርበት ከሚችለው ብስጭት እና ቁጭት በላይም አጋጣሚው በህይወቱ ካሳለፋቸው ከባድ ጊዜያቶች ውስጥ የሚጠቀስ አለፍ ሲልም ህይወቱን ሊያሳጣው የችል የነበረም ሆኖ ነው ያለፈው። መንግሥቱ እስከዚህ ጊዜ ድረስ ሀገሩን ባገለገለበት መንገድ ፣ ባስመዘገበው ውጤትም ሆነ በእግርኳስ ክህሎቱ በደጋፊው ዘንድ ምንም ያህል ተወዳጅ የነበረ ቢሆንም ዓይኑን መስዕዋት አድርጎ ግብ ያስቆጠረበት ያ ጨዋታ ግን ሕዝቡ የቀድሞው ዝናውን ረስቶ ፊቱን እንዲያዞርበት ምክንያት ሆነ።

በስታዲየም የነበረው ተመልካች መንግሥቱ የአቻነቷን ግብ ሲያስቆጥር በደረሰበት ጡጫ አንድ ዓዩን አብጦ እና ማየት ተስኖት ቡድኑ በጎዶሎ እንዳይጫወት የግዱን ጨዋታውን እንደጨረሰ አላወቀለትም። በዚያች ቅፅበት የሁሉም ደጋፊ ፍላጎት ሦስተኛ ግብ ብቻ ነበር። ይህን ኃላፊነት ደግሞ በሀሳቡ በዋነኝነት የሚጥለው መንግሥቱ ወርቁ ላይ ነው። በጨዋታው ብሔራዊ ቡድኑ ብዙ ኳሶችን ቢስትም መንግሥቱን ለሽንፈቱ ተጠያቂ ለማድረግ መነሻ የሆነው ግን አንድ ያለቀለት እና መረብ ላይ ብቻ ይጠበቅ የነበረ ኳስ ነው። በመንግሥቱ አንድበት ይህ አጋጣሚ እንዲህ ተወስቶ ነበር። ” አንድ ዓይን የለኝም ፤ ግማሽ ሜዳ ነው የማየው። የፈለገውን ያህል ብጎዳ ለውጡኝ ካላልኩ በስተቀር አልለወጥም። እንደዛ ተጎድቼ እያለሁ በከፊል ተሯሩጬ ሀገሬን ለድል የምታበቃውን 3ኛ ግብ ሁሉን ነገር ጨርሼ ኳሷን ለጌታቸው ወልዴ አቀበልኩት፡፡ ግብ አፋፍ ላይ ስለሆነች አቅጣጫ ብቻ ቀይሮ ሲነካት ግብ የምትሆን ኳስ ናት። ባዶ ጎል ላይ አንከባሎ ብቻ ማግባት የሚችላት ዓይነት ስለነበረች ሌሎቻችን ለመሳሳም እንደተዘጋጀን በዓይናችን ስንከታተል ማንም ምንም ሳይነካት ከመስመር ውጪ ወጣች፡፡ እስከ አሁን ድረስ ጌታቸውን ምን እንደነካው ሳስብ ይገርመኛል፡፡”

ከጨዋታው በኋላ በእርግጠኝነት ስሜት ድልን ይጠብቅ የነበረው ህዝብ እና የቡድኑ ኃላፊዎች ጭምር ተጫዋቾቹን ፊት መንሳት የጀመሩት ወዲያው ነበር። በሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ድል አድርገው ዋንጫ ሲያነሱ ከስታዲየም እስከ ጣይቱ ሆቴል ድረስ አብሯቸው እየጨፈረ የሸኛቸው ፣ ተሸክሞ ያጫፈራቸው ፣ እየሳመ እና ራታቸውን እያጎረሰ ደስታቸውን ያደመቀው ደጋፊ በዚህ ወቅት ግን ዓይናቸውን ማየት ሳይፈልግ ቀረ። በተለይም ደግሞ ለመንግስቱ ወርቁ ከዓይኑ እብጠት በላይ “ያንን ኳስ ራሱ ማግባት እየቻለ ለጌታቸው የሰጠው ሆን ብሎ ቡድኑ እንዲሸነፍ ነው” የሚለው ትችት የማይቋቋመው ንዴት እና ብስጭት ውስጥ ከተተው። ምሽቱን ራትም ስይበላ በህመም ፣ በለቅሶ እና በመብሰልሰል አደረ። በቀጣዮቹ ቀናትም ታሞ ሲተኛ ትችቱ በራድዮ እና በጋዜጣ ቀጥሎ ብስጭቱን ሲያባብስበት ‘ተሻለህ ወይ ?’ ብሎ ያረፈበት የሚመጣ አለመኖሩ ደግሞ ይበልጥ አሳዘነው።

እንደመንግሥቱ ላለ የወቅቱ ዝነኛ ሰው ከዚህ የበለጠ ቅጣት አልነበረም። ስሙን ከአፋቸው ከማይለዩት የዘወትር አድናቂዎቹ ጀምሮ ጫማውን እስከሚያፀዳለት ደምበኛው ድረስ ሁሉም ሰው አኮረፈው። ከእጮኛውም በቀር ማንም ያስታመመው ሰው አልነበረም ‘መንግሥቱ የት ሄደ ?’ ብሎ የጠየቀ አንድም ወዳጅ ከጎኑ አልነበረም። በዚህ ወቅት የተፈጠረበትን ስሜት ሲገልፅ “ያን ሁሉ ጊዜ ለኢትዮጵያ ኳስ መስዋዕትነት ከፍዬ የምትጠይቀኝ እጮኛዬ ሠናይት ዘሪሁን ብቻ ነበረች፡፡ በቃ እሷ ብቻ ! እጅግ በጣም ቅር አለኝ ፤ ታዋቂ ኳስ ተጨዋች መሆን ወንጀል ነው ? ብዬ አሰብኩ። የወደድኩትን ፣ የተደስትኩበትን፣ የተከበርኩበትንና ስሜ በከፍተኛ ደረጃ የተጠራበትን ያህል ኳስ ተጫዋች መሆኔን ብቻ ሳይሆን ራሴን ጠላሁ። ብቸኝነት ሰለቸኝ እና ሰው ናፈቅኩ፡፡” ይላል።

እነዚያ የብቸኝነት 15 ቀናት መንግሥቱ ቂም እንዲይዝ እና የሚያውቀውን ሰው ሁሉ እየጠላ እንዲሄድ አደረገው። ይባስ ብሎ ዓይኑን ሻል ሲለው እና ሲወጣም ከጓደኞቹ ጋር ሊቀላቀል ቢሞክር ውድድሩ አልቆ ሁለት ሣምንታት አልፈውት እንኳን አሁንም እንዳኮረፉት ነው። እሱም ታምሞ ሳይጠይቁት መቅረታቸው ሳያንስ አሁንም በፍቅር ሳይቀበሉት መቅረታቸው ይበልጥ ንዴት ውስጥ ከተተው። በዚህም የተነሳ በመጠጥ ቤቶች ከሰዎች ጋር በመጣላት ወደ ድብድብ እና ረብሻ ገባ። ጊዜ አልፎ እሱም በዕድሜ በስሎ ያንን ጊዜ ሲያስታውሰው ልክ እንዳልነበረ ቢረዳውም በዛ አፍላ ወጣትነት ጊዜው ላይ ግን ፍቅርን በመነሳቱ ሳቢያ ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ነበር። ከውድድሩ በፊት አግኝቶት የነበረውን የትምህርት ዕድል ለቡድኑ ውጤት ማማር ሲል አሳልፎ በመጨረሻ ሰው ያልለመደውን ጥላቻ ሲያሳየው ስሜቱ በእጅጉ ተጎዳ።

መንግሥቱ ከገባበት መጥፎ ስሜት በቶሎ መውጣት አልቻለም ፤ ከሰዎች ጋር መጣላቱንም ቀጠለበት። አንድ ቀን ፒያሳ አካባቢ እንዲሁ ከሰዎች ጋር ተጋጭቶ በዛ ብስጭት እና በሞቅታ ስሜት ውስጥ ለሌላ ፀብ በንዴት ወደ ንፋስ ስልክ ለመሄድ ተነሳ። በወቅቱ ይነዳው የነበረውን ሙስታንግ መኪና አስነስቶም ወደ ንፋስ ስልክ ሸመጠጠ። የያኔዋ አዲስ አበባ እንደዛሬው በመኪና ብዛት የምትጨናነቅ አልነበረችም። በዚህ ላይ ሰዓቱ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ ነው ፤ አየሩ ደግሞ ዝናባማ። ጭለማው እና የመንገዱ ጥበት ከካፊያው ጋር ተዳምሮ ለጉዞ ባይመችም መንግሥቱ ያሰበበት ቦታ ደርሶ ውስጡ የተፈጠረውን ብስጭት ለማብረድ መኪናውን በመጨረሻ ማርሽ አስፈተለካት። በቅሎ ቤት አካባቢ ሲደርስ አንድ ድንጋይ የጫነ ትሬንታ ኳትሮ መኪና በብልሽት ምክንያት ከመንገድ ቆሞ ይብቀዋል። መንግሥቱ ሜዳ ውስጥ እንደፈለጋት እንደሚያደርጋት ኳስ መኪናውን በዛ ፍጥነት ላይ ሆኖ ማዘዝ አልቻለም። በህይወት መትረፉን ተአምር በሚያደርገው ዓይነት በከባድ ሁኔታ ተጋጨ። የሚገርመው ነገር ከእንደዚህ ዓይነት አስከፊ አደጋ ተርፎም ሀሳቡ የነበረው ፀቡ ላይ እንጂ ምን እንደተፈጠረ ምን እንደገጠመው ማሰብ እንኳን አለመቻሉ ነው።

የከባድ መኪናውን ሹፌር ጨምሮ ቦታው ያኔ ጫካ እና ጨለማ በመሆኑ በአካባቢው ማንም ሰው አልነበረም። በዚያ ቅፅበት መንግሥቱ መኪናውን ከሁለት የከፈላትን አደጋ በቅጡ አልተረዳውም። ምን እንደተፈጠረም አላወቀም። ከኋላ በሳምሶናይት ያስቀመጠውን ገንዘብ ከተቀረቀረበት ስቦ አውጥቶ ከጥቅም ውጪ የሆነችውን መኪና እንደገና ለማስነሳት ይሞክራል። በወቅቱ ሞቅታው ፣ ውስጡ የነበረው ስሜት እና የተፈጠረው አደጋ ተቀላቅሎ ሁኔታውን መረዳት እንዳይችል ያደረገው ይመስላል። ያንን ታላቅ ተጫዋች በአጭር ሊያስቀረው ይችል የነበረውን አደጋ ተከትሎ በደመ ነፍስ ስላደረገው ነገር ይህንን ብሎ ነበር። “እንደገና ጋቢና ገባሁና ሞተሩን ብሞክረው እምቢ አለኝ። ያደረኩት ነጭ ሸሚዝ ነበር፡፡ በኋላም ፊት ለፊት ትልቁን መስታወቱ ሳይ የለም ፤ ‘ይሄ መኪና መስታወቱ የት ሄደ ?’ ብዬ ከመኪና ወጣሁና መሄድ ጀመርኩ። ዝም ብዬ ስሄድ ስሄድ እያዞረኝ መጣ፡፡ መንገድ መብራት ላይ ቆሜ ሸሚዜን ሳይ በደም ተጨማልቋል፡፡ ደሜ ማቆሚያ የለውም እያዞረኝ መጣ። እዚያ አካባቢ ከወደቅኩኝ በቃ አለቀልኝ እስኪነጋ አልተርፍም። ከዚያ ወደ ቡና ቤት ገባሁ። አሁን ለጊዜው ስሙ ትዝ አይለኝም፡፡ ቦታውን ግን አውቀዋለሁ፡፡አንዳንድ ጊዜ በዚያ ሳልፍ ቡና ቤቱ ትዝ ይለኛል፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ቡና ቤት ውስጥ የነበሩ ሰዎች ያውቁኛል፡፡ ሲያዩኝ በጣም ጮሁ ምክንያቱም ግንባሬ ተተርትሮ ሽማዜ ደም በደም ሆኗል፡፡ ምን እንደሆንኩ እንኳን አላውቅም፡፡ በኋላ ተሯሩጠው ወደ ሀኪም ቤት እንድሄድ አደረጉኝ፡፡ እዚያ የግሌ ዶክተር ነበር፡፡ የግንባሬን እያንዳንዱን ቦታ የሚያውቀው እርሱ ነው፡፡ እንዲሁም ጥሩ አድጎ የሚሰፋኝ እርሱ በመሆኑ ወደዚያው ሄድኩና በደምብ ሰፍቶ አዳነኝ፡፡”

መንግሥቱም በህክምና መኪናውም በኢንሹራንስ አልፈው አጋጣሚው የከፋ ችግር ሳይፈጥርበት ቢያልፍም ሰዎች ትልቅ ቦታ የሰጡት እና ሕዝብ ያከበረው የሀገር ምልክት የሆነ በፍቅር ታጅቦ የሚኖር ታላቅ ሰው በድንገት ሁሉም እንዳልነበር ሲሆን እና ብቻውን ሲቀር ሁኔታው የሚፈጥረው የስሜት ስብራት እስከምን ሊያደርስ የሚችል እንደሆነ ያሳየ ሆኖ አልፏል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!