የዘመናችን ከዋክብት ገፅ | ቆይታ ከረመዳን ናስር ጋር…

የዛሬው የዘመናችን ከዋክብት ገፅ ዕንግዳችን ረመዳን ናስር በድሬዳዋ ከተማ ልዩ ስሙ ታይዋን ሠፈር በሚባል አካባቢ ነው ተወልዶ ያደገው። እንደ አብዛኞቹ ተጫዋቾችም እግርኳስን ገና በአፍላ ዕድሜው እንደጀመረ ያወሳል። በሠፈሩ በሚገኙ ሜዳዎች ላይ የታዳጊነት ጊዜውን እያሳለፈ እያለም ኮኔል የሚባል ፕሮጀክት ውስጥ የመታቀፉን ዕድል አግኝቶ ራሱን በተሻለ ለማብቃት መስራት ጀመረ። በዚህ ፕሮጀክትም ከ13 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ ለሁለት ዓመታት እንዲሁም ከ15 እና ከ17 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ ለአንድ አንድ ዓመት ጊዜውን ካሳለፈ በኋላ የሐረር ቢራን ሁለተኛ ቡድን (B) ተቀላቀለ። በዚህ ቡድን ውስጥም ለሁለት ዓመታት ግልጋሎት ከሰጠ በኋላ በዲቪዚዮን ደረጃ ለሚወዳደረው ምስራቅ ሪጅን ቴሌ ቡድን ፊርማውን አኑሮ መጫወት ቀጠለ። ይህንን ቡድንም ከዲቪዚዮን ወደ ብሔራዊ ሊግ በማሳደግ ከክለቡ ጋር ጥሩ ጊዜን አሳለፈ።

በድሬዳዋ መቀመጫውን ያደረገው ምስራቅ ሪጅን ቴሌ ቡድን ሲፈርስ ክለብ አልባ የነበረው የዛሬው የ’ዘመናችን ኮከብ’ ረመዳን እግርኳስን ለአንድ ዓመት በመሐል በከፊል አቁሞ እንደነበር ያወሳል። እርግጥ ተጫዋቹ የሚወደውን ሙያ በወቅቱ ሙሉ ለሙሉ ባያቆምም ለመኖር ገንዘብ ያስፈልገው ስለነበር የባጃጅ ሹፌር መሆንን መርጦ በትርፍ ጊዜው በዲቪዚዮን ደረጃ ለሚወዳደሩ ክለቦች በከፊል ይጫወት ነበር። እስከ 2001 ድረስም በዚሁ የህይወት መንገድ ኑሮውን ከቀጠለ በኋላ የተሻለ ኑሮን ፍለጋ ወደ ጂቡቲ ለመሰደድ ተነሳ። እዛ በሚገኝ ዘመዱ አማካኝነት አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን ለሟሟላት እየተዘጋጀ ባለበት ሰዓትም አንድ የስልክ ጥሪ ውሳኔውን አስቀይሮ በሀገሩ እንዲቆይ አደረገው። በወቅቱ ፓስፖርቱን ጨርሶ የአየር ለውጥ ክትባት ሊወስድ ወደ ጤና ጣቢያ ሲሄድ ነበር ስልኩ ከድሬዳዋ ፖሊስ የተደወለው። ፖሊሶችም ተጫዋቹን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚደረገው የፖሊሶች የቤተሰብ ውድድር ላይ እንዲጫወትላቸው ጠይቀውት ሀሳቡን ቀይሮ ዳግም በእግርኳስ ተስፋን ሰንቆ ኑሮን ለማሸነፍ ወጠነ።

ይህንን የፖሊሶች ውድድር አዲስ አበባ መጥቶ ካከናወነ በኋላ ጥሩ ጥሩ ዕድሎችን ማግኘት የቻለው ተጫዋቹ ይበልጡን ደግሞ ወደ ብሔራዊ ሊግ የሚደረግ ውድድር ላይ ራሱን በማሳየት የብዙዎችን ቀልብ መሳብ ቻለ። በውድድሮቹ ባሳየው ብቃትም ሜታ ቢራ፣ መተሃራ ስኳር እና አየር ኃይልን ጨምሮ በርካታ ክለቦች ተጫዋቹን ለመውሰድ እንቅስቃሴ ጀመሩ። በጊዜውም ተጫዋቹ ከአይር ኃይል ጋር በመስማማት ፊርማውን በዛኑ ዓመት (2001 ክረምት) ቢያኖርም ድሬዳዋ ከተማዎች ‘እንዴት የተወለድክበትን ከተማ ጥለህ ትሄዳለህ። እኛ ጋር መተህ ፈርም’ ብለውት ከአየር ኃይል ጋር ያለውን ነገር በስምምነት በመቋጨት ወደ ድሬዳዋ በመመለስ ከ2002 ጀምሮ ቡድኑን ማገልገል ጀመረ። 2006 ላይ ወደ መቐለ ከተማ (በአሁኑ አጠራር መቐለ 70 እንድርታ) አቅንቶ ለአንድ ዓመት ግልጋሎት ከሰጠበት ዓመት ውጪም ከ2002 ጅምሮ እስከ አሁን በድሬዳዋ ከተማ ቡድን ውስጥ ይገኛል።

ረመዳን ከዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገሩን እንዲያገለገል በአሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ (ኢንስትራክተር) ጥሪ ቀርቦለት የነበረ ቢሆንም በፓስፖርት እና ሌሎች ምክንያቶች የመጫወት ዕድል ሳያገኝ ቀርቷል። ‘ዱንጋ’ እየተባለ የሚጠራው እና ለአስር ዓመታት ለድሬዳዋ ከተማ የተጫወተው ረመዳን ናስር ከሶከር ኢትዮጵያ አጫጭር ጥያቄዎች ቀርበውለት ተከታዮቹን ምላሾች ሰጥቶናል።

የእግርኳስ አርዓያህ ማነው?

ድሬዳዋ ውስጥ በጣም ብዙ እያየናቸው ያደግናቸው ተጫዋቾች አሉ። ጥሩ ብቃት የነበራቸው ነገርግን ከፍተኛ ደረጃ ሳይደርሱ የጠፉም አሉ። ግን እንደ አርዓያ ስመለከታቸው የነበሩ እና ትልቅ ደረጃ ደርሰው ከታዩት መካከል ዮርዳኖስ አባይ እና አሸናፊ ግርማን ዋነኞቹ ናቸው።

ዓምና በነበረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ላይ ጉዳት አስተናግደህ ነበር። በሁለተኛ ዙር ግን ከጉዳትህ አገግመህ ስትመጣ ነው ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ በኮቪድ ምክንያት ሊጉ የተቋተጠው። ሊጉ ከተቋረጠ በኋላ በምን ነበር ጊዜህን ስታሳልፍ የነበረው?

እንዳልከው በመጀመሪያ ዙር ውድድር ላይ በጉዳት ምክንያት አልተጫወትኩም። በሁለተኛው ዙር ውድድር ግን ከጉዳቴ አገግሜ በሁለት ጨዋታ ወደ እንቅስቃሴ ስገባ ነበር ሊጉ የተቋረጠው። ውድድሩ ከተቋረጠም በኋላ አላረፍኩም። ለረጅም ጊዜ በጉዳት ምክንያት ተቀምጬ ስላሳለፍኩት እንቅስቃሴዎችን ጥንቃቄ በታከለበት ሁኔታ ሳደርግ ነበር። ትዳር እና ልጅም ስላለ ጥንቃቄ እያደረኩ ወደ ጥሩ ብቃቴ ለመመለስ ስጥር ነው ጊዜዬ በአጠቃላይ ያለፈው።

ኮሮና ከመጣ በኋላ አዲስ የለመድከው ወይም እየለመድክ ያለህው ልማድ አለ ?

እየተጨባበጡ ሠላም አለመባባልን ለምደናል (እየሳቀ)። እንደውም በዚህ በሽታ ምክንያት መጨባበጥ ሳንረሳው እና ሳይጠፋብን አይቀርም። ዋናው ልማድ ግን ከቤተሰብ ጋር የማሳልፈው ጊዜ ነው አዲሱ ነገር። ምክንያቱም በፊት ተጫዋቾች ውድድር ስለሚኖር ለቤተሰብ ብዙ ጊዜ አይኖረንም ነበር። አሁን ግን በመጥፎ ምክንያትም ቢሆን ይህንን ልማድ አዳብረናል። በተለይ ልጄም በዚሁ ወቅት ስለሆነ ይተወለደው ከእርሱ ጋር ነበር ብዙ ጊዜ ያሳለፍኩት።

ኮቪድ-19 አሁን ጠፍቷል ወይም መድሀኒቱ ተገኝቷል የሚል ዜና ብትሰማ መጀመሪያ የምታደርገው ነገር ምንድን ነው?

ያው ከሰው ጋር መተቃቀፍ ነው። ብዙ ጊዜ ስናደርገው የነበረ ነገርግን በዚህ በሽታ ምክንያት ያቆምነው ነገር ስለሆነ ይህ ልማድ ያምራል። ስለዚህ ወዲያው ይህንን እንደሰማሁ የማደርገው መተቃቀፍ ነው። ከዚህ ውጪ የናፈቁኝ ደጋፊዎች እያዩኝ ሜዳ ላይ በነፃነት መጫወት ነው።

በትልቅ ደረጃ እንኳን ከ2002 ጀምሮ በድሬዳዋ ከተማ መጫወት ጀምረሀል። ከዛን ጊዜ ጀምሮ ምርጥ ዓመት ያሳለፍክበት ወቅት መቼ ነው?

2011 ምርጥ ጊዜ ነበረኝ። በዚህ ዓመት በግሌ ጠንካራ ልምምዶችን ሰርቼ እና ተዘጋጅቼ ነበር ወደ ውድድር የገባሁት። ከመጀመሪያው ጨዋታ ጀምሮም ድንቅ ጊዜን ነበር ያሳለፍኩት። ብዙ ጎል የሆኑ ኳሶችን አመቻችቼ አቀብያለሁ። በተጨማሪም ጎሎችን አገባ ነበር። ለዛም ነው ደግሞ የወቅቱ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ለጅቡቲው ጨዋታ የመረጠኝ። በአጠቃለይ 2011 የነበረኝ ነገር በእስካሁኑ የእግርኳስ ህይወቴም ድንቅ ዓመት ያሳለፍኩበት ነበር።

ሜዳ ላይ ያለህን ጠንካራ እና ደካማ ጎኖችህን እስቲ ንገረኝ ?

እኔ ጠንካራ ጎኔ የምለው ከኳስ ጋር ያለኝ ግንኙነት ነው። አሠልጣኞችም ከኳስ ጋር ባለኝ ነገር ብዙም እንዳስተካክል የሚነግሩኝ ነገር የለም። ደካማ ጎኔ ደግሞ ከኳስ ውጪ ያለኝ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ነው። እርግጥ ይህንን ድክመቴን ለማሻሻል እየተጋሁ ነው።

ረመዳን እግርኳስ ተጫዋች ባይሆን ምን ይሆን ነበር?

ተወልጄ ያደኩት የንግድ ቦታ በሆነው ታይዋን ሠፈር ነው። ገበያ አካባቢ ስለነበር ወደ ንግዱ ዓለም የምገባ ይመስለኛል። አልያም የባጃጅ ሹፌር ነበር የምሆነው።

አብረኸው መጫወት የምፈልገው ተጫዋች አለ?

አሁን እየተጫወቱ ካሉት መካከል ከሆነ ከይሁን እንደሻው ጋር ብጫወት ደስ ይለኛል። እርግጥ ከእርሱ ጋር ተጫውተናል። ግን አሁንም በደንብ ብንጫወት እወዳለሁ። እኔ ያለኝን እና እሱ ያለውን ነገር ሳስበው አብረን ተጣምረን ብንጫወት የተሻለ ነገር የምናመጣ ይመስለኛል።

በተቃራኒ ስትገጥመው የሚከብድህ ተጫዋቸ አለ?

እውነት ለመናገር እንዲገጥምህ የማትፈልገው ተጫዋች ይኖራል። ግን እኔ ያን ያህል የፈተነኝ ተጫዋች እስካሁን አላጋጠመኝም።

በዚህ ሰዓት በሀገራችን ከሚገኙ ተጫዋቾች ያንተን ምርጥ ተጫዋች ንገረኝ ?

ሱራፌል ዳኛቸው እና አስቻለው ታመነ በጣም ምርጥ ብቃት ላይ ነው የሚገኙት። እኔ ከምጫወትበት ቦታ አንፃር ደግሞ ሱራፌልን አስበልጣለሁ።

ይህንኑ ጥያቄ ወደ አሠልጣኞች እንውሰደው። ከአሠልጣኞችስ?

ከኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ጋር በብሔራዊ ቡድን ለአንድ ሳምንት ሰርቻለሁ። በዚያች አንድ ሳምንት እንደ እርሱ ዓይነት ተጫዋችን የሚያነሳሳ እና ተጫዋችን ለመለወጥ በቀላል እንዲሁም ግልፅ መንገድ የሚተጋ በተጨማሪም በሚገባ መንገድ ተጫዋችን የሚያሳድግ አሠልጣኝ አላየሁም። ሌሎች አሠልጣኞች ጋር ያላየሁትን እና እንደ እግርኳስ ተጫዋች የምፈልገውን ነገር እሱ ላይ አግንቸለሁ። ስለዚህ እሱ የእኔ ምርጥ አሠልጣኝ ነው።

በእግርኳስ የተደሰትክበትን አጋጣሚ አውገኝ እስኪ ?

2007 ላይ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስንገባ በጣም ነበር የተደሰትኩት። የድሬዳዋን ህዝብ ደስታ በዓይኔ ያየሁበት ልዩ ወቅት ስለነበር ያንን ጊዜ መቼም አልረሳውም።

በተቃራኒ በእግርኳስ የተከፋህበትስ አጋጣሚ አለ ?

2004 ላይ ድሬዳዋ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ወደ ታችኛው ሊግ ሲወርድ በጣም ነበር የተከፋሁት። የድሬዳዋን የእግርኳስ አፍቃሪ ያሳዘነ ክስተት ስለነበር እኔም ተከፍቼ ነበር።

እግርኳስ ካቆምክ በኋላ በምን ሙያ ለመዝለቅ ታስባለህ?

ወደ ንግዱ ዓለም የምገባ ይመስለኛል። ቅድም እንዳልኩት አካባቢዬ ለገበያ እና ለንግድ ቅርብ ስለነበር እኔም ወደ ነጋዴነቱ የምገባ ይመስለኛል።

“ዱንጋ” የሚል ቅፅል ስም አለህ። ማን ነው ያወጣለህ ? ለምንስ ዱንጋ ተባልክ ?

ከረጅም ዓመታት በፊት እንደ ቤተሰብ የምናየው ዑመር የሚባል ጎረቤታችን ነበር። እና ይህ ሰው በጊዜው አዘውትሬ የምለብሳትን 8 ቁጥር የታተመባት ቢጫ መለያ በማየት ዱንጋ ብሎ ሰየመኝ። እኔ ያዛኔ ዱንጋ ማን ይሁን ማን አላውቅም ነበር። ከዛ ግን እሱ ያወጣልኝ ይህ ቅፅል ስም ፀንቶ እስካሁን እየተጣራሁበት ይገኛል።

የቤተሰብ ህይወትህ ምን ይመስላል? በመልሶችህ መካከል ስለ ልጅህ ስታነሳ ነበር።

በአሁኑ ሰዓት በጣም ከምወዳት ባለቤቴ ጋር ነው እየኖርኩ ያለሁት። ሻህር ረመዳን የሚባል ወንድ ልጅም ወልዳልኝ ህይወታችን በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው። በአጠቃላይ በጣም ደስ የሚል ህይወት ነው እየመራሁ የምገኘው።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!