ከፍተኛ ሊግ | ሀላባ ከተማ ሁለት ተጫዋቾችን አስፈረመ

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ ላይ የሚገኘው ሀላባ ከተማ በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን እያስፈረመ እንዲሁም የነባር ተጫዋቾችን ኮንትራት እያራዘመ የሚገኝ ሲሆን አሁን ደግሞ ተጨማሪ ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል፡፡

ከፈራሚዎቹ መሐል ግብ ጠባቂው ቢሊንጌ ኢኖህ ተጠቃሽ ነው፡፡ ግዙፉ ካሜሩናዊ የቀድሞው መቐለ፣ ወልዲያ እና ወልቂጤ ከተማ ግብ ጠባቂ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ረጅም አመት ቆይታ ካላቸው የውጪ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ሲሆን የተሰረዘውን የውድድር አመት በሀዋሳ ከተማ ካሳለፈ በኃላ በወልቂጤ አብሮ መስራት ወደቻለው አሰልጣኝ ደረጀ በላይ ክለብ በአንድ ዓመት ውል አምርቷል፡፡

ሌላኛው ፈራሚ የመስመር አጥቂው ዳንኤል ዳዊት ነው፡፡ ይህ የነቀምቴ ከተማ ተጫዋች ወላይታ ድቻን ዓምና ተቀላቅሎ የነበረ ቢሆንም በዓመቱ አጋማሽ ከክለቡ ጋር ተለያይቶ ከቆየ በኃላ ወደ ቀድሞ ክለቡ ነቀምቴ ቢመለስም ኮቪድ 19 ወደ ሀገራችን በመግባቱ ጨዋታ ሳያደርግ ከክለቡ ጋር ተለያይቶ ሀላባን ተቀላቅሏል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉ሳንዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!