በዘንድሮ ፕሪምየር ሊግ ስንት ክለቦች ይወርዳሉ?

በ13 ክለቦች መካከል ለመደረግ የተቃረበው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ወራጅ እና በ2014 ውድድር ለመሳተፍ ከከፍተኛ ሊግ የሚያድጉ ክለቦች ስንት እንደሆኑ ታውቋል።

በትግራይ ክልል መቀመጫቸውን ያደረጉት መቐለ 70 እንደርታ፣ ወልዋሎ ዓ/ዩ እና ስሑል ሽረ በ2013 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር የመሳተፍ እድል እጅግ ጠባብ መሆኑን ተከትሎ ሊጉን በበላይነት የሚያስተዳድረው የሊጉ አክሲዮን ማኅበሩ አማራጭ የሊግ መርሐ-ግብር ማውጣቱን መዘገባችን ይታወሳል። ያለ ሦስቱ የትግራይ ክለቦች በወጣው የ13 ክለቦች የጨዋታ መርሐ-ግብር መሠረትም በውድድር ዓመቱ 156 ጨዋታዎች ይደረጋሉ። 

ከሰዓታት በፊት የወጣውን አዲስ መርሐ-ግብር ተከትሎም የተለያዩ የስፖርት ቤተሰቦች በሊጉ ስንት ክለቦች ወደ ታችኛው የሊግ እርከን (ከፍተኛ ሊግ) እንደሚወርዱ ሲጠይቁ ነበር። ይህንን ተከትሎም ሶከር ኢትዮጵያ የሚመለከተውን አካል ጠይቆ በተረዳው መሠረት ያለምንም ለውጥ በ2013 የውድድር ዓመት ሦስት ክለቦች ባስመዘገቡት ውጤት መሠረት ወደ ታችኛው የሊግ እርከን እንደሚወርዱ አረጋግጠናል። ስለዚህ በደረጃ ሰንጠረዡ 13፣12 እና 11ኛ ደረጃን ይዘው የሚያጠናቅቁ ክለቦች ወደ ከፍተኛ ሊግ ይወርዳሉ።

ሦስቱ ክለቦች ወደ ሁለተኛው የሊግ እርከን ከወረዱ በኋላ በ2013 የከፍተኛ ሊግ ውድድር የየምድቦቻቸው አንደኛ የሆኑ ሦስት ክለቦች እንደ ወትሮ ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲያድጉ ይደረጋል። ከእነርሱ በተጨማሪ በ2013 ውድድር እንደማይሳተፉ የሚጠበቀው መቐለ 70 እንደርታ፣ ወልዋሎ ዓ/ዩ እና ስሑል ሽረ ሊጉን ዳግም ተቀላቅለው የ2014 የውድድር ዘመን በ16 ክለቦች መካከል መደረግ ይጀምራል።

© ሶከር ኢትዮጵያ