ወላይታ ድቻዎች ከአንድ ሳምንት ልምምድ ማቆም በኋላ ዳግም ተመልሰዋል

ወላይታ ድቻዎች ከቀናት ቆይታ በኃላ ወደ መደበኛ ልምምዳቸው ተመልሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሊጀመር በጣት የሚቆጠር ቀን እየቀረው የሊጉ ክለቦች ለተጫዋቾቻቸው ደመወዝ ለመክፈል እየተቸገሩ አልፎም ደግሞ ተጫዋቾች ችግራችን ካልተቀረፈ በሚል ልምምዳቸው እያቆሙ ይገኛሉ፡፡ ይህ ችግር ጎልቶ ከሚታይባቸው ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ወላይታ ድቻ ሁለት ጊዜያትን ያህል ልምምድ ለማቋረጥ ተገዶ ሰንብቷል፡፡ በተለይ ሁለተኛውን ልምምድ ያቋረጠበት መንገድ ሰፊ ቀኖች የወሰደ ነበር፡፡ የክለቡ ተጫዋቾች የአምስት ወር ደመወዝ አልተከፈለንም በማለት ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ሀዋሳ ላይ ከሲዳማ ቡና ጋር ካደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ በኃላ ለተከታታይ ስምንት ቀናት ያህል ተጫዋቾቹ ካልተከፈለን አንሰራም ብለው ከቆዩ በኃላ በዛሬው ዕለት ሁሉም ተጫዋቾች የሦስት ወር ደመወዝ ተፈጻሚ ስለሆነላቸው ወደ መደበኛ ልምምዳቸው ተሟልተው ተመልሰዋል፡፡

ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የፊታችን ቅዳሜ የሚጀመር ሲሆን ወላይታ ድቻ ሰኞ ሀድያ ሆሳዕናን በመጀመሪያ ጨዋታው የሚገጥም ይሆናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ