“ወደፊት ራሴን በትልቅ ደረጃ ማሳየት አስባለው” ተስፈኛው ወጣት ፍራኦል ጫላ

በአጭር በሆነው የአዳማ የታዳጊ ቡድን ቆይታው በአስደናቂ ሁኔታ ጎል የማስቆጠር አቅሙን እያሳየ የሚገኘው ፍራኦል ጫላ የዛሬው ተስፈኞች አምድ እንግዳችን ነው።

ለበርካታ ተስፈኛ እግርኳስ ተጫዋቾች ዕድል በመስጠት በሚታወቀው አዳማ ከተማ ከ2011 ጀምሮ በሁለቱም የዕድሜ እርከኖች ማለትም ከ17 እና 20 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ ተጫውቷል። በተለይ በ2011 በአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን አወዳዳሪነት በሚካሄደው ከ17 ዓመት በታች ውድድር ላይ ባሳየው አስደናቂ የጎል አጨራረስ ብቃቱ በ28 ጎሎች የውድድሩ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን አጠናቋል።

በተደጋጋሚም ሶከር ኢትዮጵያ ተገኝታ በዘገበችበት የታዳጊዎች ውድድር የዚህን ታዳጊ አቅም እና ወደፊት ትልቅ ደረጃ መድረስ የሚያስችል ተስፋን መግለፃችን ይታወቃል።

ይህ አዳማ ቀበሌ 01 የተወለደው ወጣት ተጫዋች ፍራኦል ጫላ ይባላል። ለቤተሰቡ ብቸኛ ወንድ ልጅ ሲሆን የጀመረው የእግርኳስ ህይወቱ በአሁን ሰዓት በአዳማ ከ20 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ እየተጫወተ ይገኛል። በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የአሰልጣኝነት ዘመን ዓምና ከዋናው ቡድን ጋር በመቀላቀል ዝግጅት ሲገባ በዘንድሮ ዓመት ከሚያድጉ ተጫዋቾች አንዱ ይሆናል ቢባልም እስካሁን ይሄ ሳይሳካ ቀርቷል። በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና በቅርቡ በሴካፋ ዋንጫ በተካፈለው ቡድን ይካተታል ቢባልም አለመካተቱ አስገራሚ ሆኗል። ወደ ፊት እራሱን ጠብቆ የነገውን ተስፋ እያሰበ ጠንክሮ በመስራት መዝለቅ ከቻለ ትልቅ ተጫዋች መሆን ይችላል ብለን ከወዲሁ የምንናገርለት ተስፈኛው አጥቂ ፍራኦል ጫላ የዛሬው ተስፈኛ አምዳችን በመሆን ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተው አሰናድተን አቅርበነዋል።

” ተወልጄ ባደኩበት አዳማ ከተማ ቀቤሌ 01 ታቦት ፍሬ በሚባል ሜዳ ነው ስጫወት ያደኩት። ከቤተሰቤ እግርኳስን ተጫውቶ ያለፈ ሰው ባይኖርም ከልጅነቴ ጀምሮ እግርኳስ እወድ ስለነበረ መጫወት የጀመርኩት እድሜዬ ከፍ ሲል ቃልአብ ፋኖ የሚባል የሰፈር ቡድን ነበር መጫወት ጀመርኩኝ እዛ እያለው ለኦሮሚያ ከ17 ዓመት በታች ምርጥ ተመልምዬ በ2010 ተመረጥኩኝ። በመቀጠል ኦሮሚያን ወክዬ ለመላው ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ተመርጬ ስጫወት የነበረኝን ጥሩ እንቅስቃሴ አይተው በ2011 ለአዳማ ከ17 ዓመት በታች ቡድን ልገባ ችያለው። ያው ሁሉም እንደሚያቀው በአዲስ አበባ በተካሄደው ከ17 ዓመት በታች ውድድር ላይ ጥሩ ጊዜ በማሳለፍ በሀሌታ፣ በሠላም እና በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ሐትሪክ በመስራት በአጠቃላይ በሁሉም ጨዋታ 28 ጎል አስቆጥሬ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ለመሸለም ችያለው። ለኔ ለእግርኳስ ህይወቴ ለወደ ፊቱ ተስፋ የጣልኩበት ብዙ መስራት እንዳለብኝ ያወኩበት፣ እራሴን እንደጠበኩት፣ እንዳሰብኩት ያገኘሁት ጎልቼ እንድወጣ ያደረገኝ ውድድር ነበር። ጎል የማስቆጠር አቅሜን ከቃለአብ ፋኖ የሚባል አሰልጣኝ አለ እርሱ ከድሮም ጀምሮ በደንብ ስላሰራኝ ያገኘሁት ይመስለኛል። የሚገርመው ለብቻዬ ለይቶ ሁሉ ያሰራኝ የነበረ ጎበዝ አሰልጣኝ ነው። በ2012 ከሃያ ዓመት በታች ቡድን አደኩ፤ ውድድሩ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስም ጥሩ ቆይታ አድርጌ ነበር። ስለ ወደፊቱ በመጀመርያ አዳማን ማገልገል እፈልጋለሁ። ራሴን በትልቅ ደረጃ ማሳየት አስባለው። እድሉን ካገኘሁኝ ከሀገር ውጭ ሁሉ ወጥቶ የመጫወት ከፍተኛ ፍላጎት አለኝ። የሀገሬን ብሔራዊ ቡድን ማልያ መልበስን አስባለሁ። ለዚህም በምችለው አቅም እየሰራሁ ነው። በመጨረሻም ለኔ እዚህ መድረስ ብዙ የማመሰግነው ሰው አለ። ከሁሉ አስቀድሜ አሰልጣኜ ቃልአብ ፋኖን አመሰግናለሁ። ቤተሰቦቼ በጣም ነው የሚረዱኝ በተለይ አባቴን አመሰግናለሁ። የአዳማ የታዳጊ ቡድን አሰልጣኞቼን በሙሉ አመሰግናለው።


© ሶከር ኢትዮጵያ