ሰበታ ከተማ አራት ተጫዋቾችን አስፈረመ

ሰበታ ከተማ አራት ተጫዋቾችን በዛሬው ዕለት ሲያስፈርም ከዘጠኝ ተጫዋቾች ጋር ደግሞ ተለያይቷል።

በተጫዋቾቻቸው ከሰሞኑ ከደመወዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ጥያቄ ሲነሳባቸው የነበሩት ሰበታ ከተማዎች ከተለያዩ አካላት እያደረጉት ካለው የገቢ ማሰባሰብ ስራ አንፃር ዛሬ እንደሚፈፅሙ ይጠበቃል። ሆኖም ክለቡ በስምምነት በለቃቃቸው ነባር ተጫዋቾች ምትክ አራት ተጫዋቾችን በዛሬው ዕለት አስፈርሟል፡፡ በዚህም ያሬድ ሀሰን፣ ዓለማየሁ ሙለታ፣ አብዱልባሲጥ ከማል እና ቃልኪዳን ዘላለም አዲስ ፈራሚዎች ሆነዋል።

የግራ መስመር ተከላካይ እና አማካይ ቦታ ላይ የሚጫወተው ያሬድ ሀሰን በወልዲያ፣ መቐለ 70 እንደርታ እና ያለፈውን ዓመት ደግሞ በድሬዳዋ ተጫውቶ አሳልፏል። ሌላኛው ፈራሚ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ዓለማየሁ ሙለታ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድን እስከ ዋናው እንዲሁም በኢትዮጵያ ቡና እና አዲስ አበባ ከተማ ተጫውቶ አሳልፏል፡፡ ሌሎቹ ፈራሚዎች ደግሞ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም የተሰረዘውን የውድድር ዓመት በከፍተኛ ሊጉ ደደቢት ሲጫወቱ የቆዩት አማካዩ አብዱልባሲጥ ከማል እና አጥቂው ቃልኪዳን ዘላለም ሆነዋል፡፡

ከክለቡ ጋር በተያያዘ በኃይሉ አሰፋ (ቱሳ)፣ ሳሙኤል ታዬ፣ ፍርዳወቅ ሲሳይ፣ ታደለ ባይሳ እና ሌሎች አምስት ተጫዋቾች ጋር በስምምነት ተለያይቷል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ