ቅድመ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና ከ ወልቂጤ ከተማ

በሊጉ የሁለተኛ ቀን ውሎ መክፈቻ ላይ የሚደረገውን ጨዋታ የተመለከቱ ጉዳዮችን አንዲህ አንስተናል።

ከጥቅምት ሰባት ጀምሮ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ሲያደርግ የሰነበተው ኢትዮጵያ ቡና በተሰረዘው የውድድር ዓመት የጀመረውን የአጨዋወት ዘይቤ የሚያቀጥልበትን ጅማሮ ያደርጋል። ከአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ጋር ዘላቂ ዕቅድን ይዞ እየሰራ የሚገኘው ቡና ከቁልፍ ተጫዋቾቹ ጋር የረጅም ጊዜ ቃልኪዳን በማሰር የቡድን ግንባታውን መስመር ለማስያዝ ሞክሯል። በዝውውር መስኮት ተሳትፎውም ያሉበት ክፍተቶች ላይ ብቻ ትኩረት ያደረጉ ዝውውሮችን ነው ያከናወነው። በግብ ጠባቂ እና የኋላ መስመሩ ላይ አማራጩን ያሰፋለት እና በሊጉ ልምድ አላቸው የሚባሉ ተጫዋቾች ላይ ያተኮረ በሚመስል መልኩ አቤል ማሞ፣ አበበ ጥላሁን እና ዘካርያስ ቱጂን አስፈርሟል። በተለይም የፈቱዲን ጀማል መልቀቅን ተከትሎ የሚፈጠረውን ክፍተት ለመሸፈን የአበበ መምጣት የተመጣጠነ አተካክ እንደሆነ መናገር ይቻላል። በቁጥር በበዙ ዝውውቶች በቡድኑ መዋቅር ላይ በርካታ ለውጦች አለማድረጉ ቡናን ሊጠቅመው እንደሚችል መገመትም አይከብድም። ከዛ ውጪ በበርካታ ደጋፊዎቹ ፊት እንዳይጫወት ኮቪድ እክል ሊሆንበት ቢችልም በአመዛኙ ወጣት የሚባለው ስብስቡ ከአሰልጣኙ አጨዋወት ጋር ጫና በሌለው ከባቢ ውስጥ ከሁኔታዎች ጋር ተስማምቶ እንዲሄድ ተጠቃሚ ሊያደርገው እንደሚችልም ይገመታል።

ዐምና ወደ ፕሪምየር ሊጉ መጥቶ ጥሩ ሲንቀሳቀስ ታይቶ የነበረው ወልቂጤ ውድድሩ መሰረዙን ተከትሎ አጭር ልምድ በቀመሰበት ውድድር ላይ ዳግም ተደራጅቶ ለመመለስ ዕድል አግኝቷል። ለዚህም ይመስላል ክለቡ በርካታ ተጫዋቾችን ካስፈረሙ ክለቦች መካከል እንዲመደብ ያደረጉትን አዳዲስ ተጫዋቾች ያስመጣው። እንደ ሥዩም ተስፋዬ፣ ፍሬው ሰለሞን፣ አሚን ነስሩ፣ ዮሀንስ በዛብህ፣ ሀብታሙ ሸዋለም የመሳሰሉ ተጫዋቾችን ማምጣቱ አምና በውድድሩ ላይ የታየበትን የእንግድነት ስሜት እንዲቀንስ የሚያስችለው ነው። በሌላ በኩል ጠንካራ ጎኑ የነበረው ጫላ ተሺታን ማጣቱን በውሰት ከመጣው አሜ መሀመድ በተጨማሪ ሄኖክ አየለ፣ አቡበከር ሳኒ፣ ተስፋዬ ነጋሽ ዓይነት ተጫዋቾችን በማስፈረም የፊት መስመሩን ይበልጥ ለማጠናከር ያለመም ይመስላል። ከዚህ በተጨማሪ ወልቂጤዎች ያሬድ ታደሰ እና ረመዳን የሱፍ በእጃቸው አስገብተዋል። በእርግጥም የዝውውሮቹ መበራከት ከጥቅምት አጋማሽ ጀምሮ ቡድናቸውን ሲያዘጋጁ ለነበሩት አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የውህደት ስራቸውን ሊያከብድባቸው እንደሚችል ማሰብ ይቻላል። የነገው የቡድኑ የመጀመሪያ ጨዋታ ደግሞ በተቃራኒው በቡድኑ ላይ ብዙ ለውጥ ካላደረገው ኢትዮጵያ ቡና ጋር መሆኑ የውህደት ፈተናውን ከፍ ሊያደርገው ይችላል።

ሁለቱ ቡድኖች በተሰረዘው የውድድር ዓመት ተገናኝተው 1-1 የተለያዩበትን ጨዋታ ሳያካትት በቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን ያደርጋሉ። ወልቂጤ ከተማ በአብዛኛው አዲስ ፈራሚዎቹን እንደሚጠቀም በሚጠበቅበት በዚህ ጨዋታ በሁለቱም ተጋጣሚዎች በኩል የተሰማ የጉዳት ዜና የለም።


© ሶከር ኢትዮጵያ