ሪፖርት | ወልቂጤ ከተማ ከመመራነት ተነስቶ ከኢትዮጵያ ቡና ነጥብ ተጋርቷል

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ የጨዋታ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ ረፋድ ላይ በተደረገ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ በሁለት ጎል ልዩነት ከመመራት ተነስቶ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነጥብ ተጋርቷል።

ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል በሜዳው የላይኛው ክፍል ኳስን መልሶ ለማግኘት በሁለቱም በኩል ሙከራዎችን በስፋት ያስመለከተ ነበር። በተለይም በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተደጋጋሚ ጥረቶችን ተመልክተናል።

በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የተደረጉት ተጠቃሽ ሙከራዎች በመሰል ሒደት የተገኙ ነበሩ። በኢትዮጵያ ቡና በኩል በ7ኛው ደቂቃ እንዳለ ደባልቄ ሞክሮ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት እንዲሁም ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን ሞክሮ ጀማል የያዘበት ኳስ ማሳያ ናቸው።

በወልቂጤ ከተማዎች በኩል በፍሬው ሰለሞን የሚመራው የጫና ሒደት በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮችን ለስህተት ሲዳርግ ተስተውሏል። በዚህም ከአቤል ማሞ እና አበበ ጥላሁን የመቀባበል ስህተት የተገኙትን አጋጣሚዎች አህመድ ሁሴን እና አብዱልከሪም ወርቁ በአስቆጭ ሁኔታ መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል።

ከእረፍት መልስ ጨዋታው ሲቀጥል በ50ኛው ደቂቃ ላይ ተስፋዬ ነጋሽ አቡበከር ናስር ላይ በሰራው ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ራሱ አቡበከር ናስር በማስቆጠር ኢትዮጵያ ቡናን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከግቧ መቆጠር ወዲህ ኢትዮጵያ ቡናዎች ሁለት ፍፁም ያለቀላቸው አጋጣሚዎችን ቢያገኙም በአስገራሚ መልኩ አቡበከር ናስር እና እንዳለ ደባልቄ መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። ነገርግን በ66ኛው ደቂቃ በወልቂጤ ከተማ ተጫዋቾች መዘናጋት የተገኘውን ኳስ አቡበከር ናስር በጀማል ጣሰው ጉዳት ተቀይሮ በገባው ጆርጅ ደስታ መረብ ላይ አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት ከፍ ማድረግ ችሏል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ ቡናዎች ጨዋታውን የተቆጣጠሩ ቢመስልም ወልቂጤ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት ጥሩ ጥሩ እድሎችን ፈጥረዋል። በ74ኛው ደቂቃም ተቀይሮ የገባው ያሬድ ታደሰ ወልቂጤን ወደ ጨዋታ የመለሰች ግብ አስቆጥሮ የቡድኑን ተነሳሽነት ከፍ ማድረግ ችሏል።

በዚች ግብ ይበልጥ የተነቃቁት ወልቂጤ ከተማዎች በ90ኛው ደቂቃ ላይ ረመዳን የሱፍ ራሱ ያስጀመረውን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ የተገኘውን አጋጣሚ በማስቆጠር ቡድኑን ከመመራት ተነስቶ ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አስችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ