ቅድመ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና ከ ሀዲያ ሆሳዕና

የሦስተኛውን ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ እንዲህ ዳሰነዋል።

ሲዳማ ቡና ካለ አዲስ ግዳይ ምን ዓይነት መልክ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል በተጠበቀበት ጨዋታ ደካማ አጀማመር አድርጓል። ምንም እንኳን ከአማካይ ክፍሉ በቂ ግልጋሎት ባያገኝም እንደተፈራውም በማጥቃቱ ረገድ የተቸገርበትን ጨዋታ ነበር ከባህር ዳር ጋር ያደረገው። በእርግጥ እንደጫላ ተሺታ ዓይነት አዲስ ፈራሞዎችን አለመጠቀሙ ችግሩን ሊያስተካክል የሚችልበትን ዕድል ያሰፋዋል። ከሁሉም በላይ ግን አማካይ ክፍሉ ላይ የታየው በተጋጣሚ ቁጥጥር ስር የመውደቅ ችግር እንደ ነገ ዓይነት ጨዋታዎች ላይ ካልታረሙ ለቡድኑ ችግር መሆናቸው አይቀርም። ከሽንፈት እንደመጣ እና በቶሎ ማሸነፍ እንዳለበት ቡድን አጥቅቶ ለመጫወት እንደሚሞክር የሚጠበቀው ሲዳማ በመከላከሉ ጠንካራ ሆኖ የታየው የነገ ተጋጣሚውን በቅብብሎች የመስበር ግዴታ ይኖርበታል። ይህን ለማድረግ የዳዊት ተፈራ እንቅስቃሴ ላይ የተመረኮዘውን የቡድኑን የኳስ ፍሰት ማመጣጠን እና የቀደመውን ጠንካራ ጎኑ የሆነውን የመልሶ ማጥቃት እና ቀጥተኛ ኳሶን የመጠቀም አዝማሚያ ከግምት ሊያስገባ እንደሚችል ይገመታል።

ሁለቱንም ጨዋታዎቹን በድል መወጣት የቻለው ሀዲያ ሆሳዕና ነገ ለሦስተኛ ጊዜ ሙሉ ነጥብ ለማግኘት ወደ ሜዳ ይገባል። በጨዋታዎቹ ቡድኑ በጠንካራ የመከላከል መሰረት ላይ እንደተገነባ በአራትም በሦስትም የኃላ መሰመር ተሰላፊዎች ተጠቅሞ ማሳየት ችሏል። በማጥቃቱ ረገድ ግን አሁንም ክፍተቶች እንዳሉበት ይታመናል። በተለይም በዳዋ ሆቴሳ የግል ብቃት ላይ የተመረኮዘ ሆኖ የታየው የፊት መስመሩ ነገ ዳዋ በሌለበት ጨዋታ ሊፈተን እንደሚችል ይገመታል። ከተጋጣሚው አንፃር ያለብዙ ጫና ወደ ሜዳ እንደሚገባ የሚጠበቀው ሆሳዕና በጨዋታው ጥንቃቄ እንደማይለየው ቢገመትም መሀል ሜዳ ላይ የሲዳማ አማካዮችን ለመቆጣጠር ከሚያደርገው ጥረት ባለፈ እንደ ካሉሻ አልሀሰን ላሉ ፈጣሪ አማካዮቹ ከፍ ያለ ደቂቃን በመስጠት ቡድኑ የተስተዋለበትን የፈጠራ ችግር ለማቃለል እንደሚሞክር ይታሰባል።

አራት የሚደርሱ ተጫዋቾቹን በኮሮና ምክንያት በማይጠቀመው የሲዳማ ቡና የቡድን ስብስብ ውስጥ ዮሴፍ ዮሃንስም አልተካተተም። በሀዲያ ሆሳዕና በኩል የተሰማ የጉዳት ዜና የሌለ ሲሆን ዳዋ ሆቴሳ ግን በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ቅጣት ጨዋታው ያልፈዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ በተገናኙበት የ2008 የውድድር ዓመት ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ሆሳዕና ላይ 1-1 ሲለያዩ ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና 1-0 አሸንፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

መሳይ አያኖ

አማኑኤል እንዳለ – ግርማ በቀለ – ፈቱዲን ጀማል – ግሩም አሰፋ

ዳዊት ተፈራ – ያስር ሙገርዋ – አበባየሁ ዮሃንስ

ይገዙ ቦጋለ – ማማዱ ሲዲቤ – ሀብታሙ ገዛኸኝ

ሀዲያ ሆሳዕና (4-3-3)

መሀመድ ሙንታሪ

ሱለይማን ሀሚድ – እሴንዴ አይዛክ – ቴዎድሮስ በቀለ – ሄኖክ አርፌጮ

አዲስ ህንፃ – ተስፋዬ አለባቸው – አማንኤል ጎበና

ዱላ ሙላቱ – ሳሊፉ ፎፋና – ቢስማርክ አፒያ


© ሶከር ኢትዮጵያ