ሪፖርት | የሀዲያ ሆሳዕና የድል ጉዞ ቀጥሏል

የውጪ ዜጎች በደመቁበት ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕና ሲዳማ ቡናን 3-1 ማሸነፍ ችሏል።

በሁለተኛው ሳምንት አራፊ የነበረው ሲዳማ ከባህር ዳር ሽንፈቱ ጊት ጋትኮችን በአማኑኤል እንዳለ አዲሱ አቱሳን በማማዱ ሲዲቤ ተክቶ ጨዋታውን ጀምሯል። ሀዲያ ሆሳዕና ባህር ዳርን ሲረታ ከተጠቀመበት ቡድን ውስጥ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ቴዎድሮስ በቀለ ፣ አዲስ ህንፃ እና በቅጣት የሌለው ዳዋ ሆቴሳን በካሉሻ አልሀሰን፣ ዱላ ሙላቱ እና ሳሊፉ ፎፋና ተክቷል።


የተመጣጠነ ፉክክር በተመለከትንበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች የማጥቃት እና ዕድሎችን የመፍጠር ፍላጎት ኖሯቸው ታይተዋል። 2ኛው ደቂቃ ላይ አልሀሰን ካሉሻ ከሱለይማን ሀሚድ ተቀብሎ ከሳጥን ውጪ በሞከረው እና አግዳሚው በመለሰበት ኳስ ግብ የማግኘት ጥረታቸውን የጀመሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች 15ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። በተከላካዮች ጥምረት በተገኘው ጎል ሄኖክ አርፌጮ ከማዕዘን ያሻማውን አይዛክ ኢሴንዴ በግንባር በመግጨት ማስቆጠር ችሏል። ሀዲያዎች በቀጥተኛ ኳሶች ወደ ግብ ለመድረስ በጣሩባቸው ቀጣይ ደቂቃዎች አልፎ አልፎ ከቆሙ ኳሶች በመነሳት የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር የሞከሩ ሲሆን ሁለተኛ ግብ ግን አላገኙም።


መሀል ሜዳ ላይ የነበረውን ፍትጊያ በተወሰኑ አጋጣሚዎች ብቻ ማለፍ የቻሉት ሲዳማዎችም ፊት መስመር ላይ መረጋጋት አልታየባቸውም። መጀመሪያ አካባቢ በሀዲያ ሆሳዕናው ግብ ጠባቂ መሐመድ ሙንታሪ ስህተት ያገኙትን አጋጣሚ መጠቀም የተሳናቸው ሲዳማዎች 23 ኛው ደቂቃ ላይ አዲሱ አቱላ ከሀብታሙ ገዛኸኝ የተላከለትን ኳስ በቀጥታ ሞክሮ ሲወጣበት 36ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ዳዊት ተፈራ ያደረሰውን ኳስ ሀብታሙ ሞክሮ ሙንታሪ ይዞበታል።

ሁለተኛው አጋማሽ እንደጀመረ ሀዲያ ሆሳዕናዎች የግብ ልዩነቱን ማስፋት ችለዋል። ወደ ቀኝ መስመር ያደላ የቅጣት ምት አግኝተው አልሀሰን ካሉሻ ያሻማል ተብሎ ሲጠበቅ ለቢስማርክ አፒያ አሳልፎለት አጥቂው አምልጦ በመውጣት አስቆጥሯል። የውጪ ተጫዋቾች ጥምረት 56ኛው ደቂቃ ላይም ለሀዲያ ሆሳዕና ሦስተኛ ግብ አስገኝቶለታል። ካሉሻ ከተከላካዮች መሀል ያሳለፈለትን ኳስ ፎፋና ፍጥነት እና ጉልበቱን ተጠቅሞ ፈቱዲን ጀማልን በማለፍ ቀለል ባለ አጨራረስ ልዩነቱን አስፍቷል።

ጫላ ተሺታን ቀይረው በማስገባት የማጥቃት ኃይላቸውን ለመጨመር ጥረት ያደረጉት ሲዳማዎች በሀዲያ ሳጥን ውስጥ አስፈሪነታቸው ተሻሽሎ ባይታይም 78ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት በተነሳ እና በተጨራረፈ ኳስ መነሻነት ጊትጋት ኮች አስቆጥሮላቸዋል። ግቡን ተከትሎ ከይገዙ ቦጋለ ጋር ግብ ግብ የፈጠረው የሀዲያው ግብ ጠባቂ መሐመድ ሙንታሪም የአርቢትር እያሱ ፈንቴ ቀይ ካርድ ሰለባ ሆኗል።

ስምንት ተጨማሪ ደቂቃዎችን ባስተናገደው ጨዋታ ሀዲያዎች ሙሉ ለሙሉ ወደ ኋላ በማፈግፈግ ከሀብታሙ ገዛኸኝ የርቀር ሙከራ ውጪ ሌላ አደጋ ሳይጋረጥባቸው ጨዋታውን አገባደዋይዞበታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ