“የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ለኛ በጣም ያስፈልገን ነበር” – ዳዊት ተፈራ

ዛሬ ረፋድ ላይ ሲዳማ ቡና የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ድል እንዲያሳካ ብቸኛውን ጎል በፍፁም ቅጣት ምት ያስቆጠረው እና በጨዋታው ጥሩ ከተንቀሳቀሰው ዳዊት ተፈራ ጋር ቆይታ አድርገናል።

በሻሸመኔ ተወልዶ የእግርኳስ ህይወቱን በመከላከያ ታዳጊ ቡድን የጀመረው ዳዊት ተፈራ ወደ ጅማ አባ ቡና ካመራ በኋላ ስኬታማ ዓመታትን አሳልፏል። ጅማ አባ ቡና ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሲቀላቀል የእርሱ አስተዋፆኦ የጎላ የነበረው ዳዊት በተለይ በአባ ቡና ታሪክ የመጀመርያውን የፕሪምየር ሊግ ጎል በማስቆጠር ስሙን መፃፍ ችሏል። በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን መጫወት ቢችልም በዋናው ብሔራዊ ቡድን ከመጠራት በዘለለ በቂ አገልግሎት ለመስጠት አልታደለም። በሰውነቱ ደቃቃ በቁመቱ አጭር ቢሆንም ሜዳ ውስጥ ያለው ክህሎት፣ በራስ መተማመኑ እና የመጫወት ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው።

ዳዊት ሲዳማ ቡናን ከተቀላቀለ ጊዜ ጀምሮ አስገራሚ አቋሙን እያሳየ የሚገኝ ሲሆን በዘንድሮ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሲዳማ ቡና በተከታታይ ሦስት ጨዋታ ድል አለማድረጉን ተከትሎ ቡድኑ ፈተና ውስጥ የነበረ ቢሆንም በዛሬው ዕለት ከድል ጋር የታረቁበትን ውጤት ሲያስመዘግቡ ወልቂጤዎች ላይ ብቸኛውን የማሸነፊያ ጎል በፍፀም ቅጣት ምት በማስቆጠር ለቡድኑ እፎይታ ሰጥቷል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ስለጨዋታው እና በቀጣይ በሊጉ ስለሚኖረው ጉዞ አዋርተነው ተከታዩን መልስ ሰጥቶናል።

“የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ለእኛ በጣም ያስፈልገን ነበር። በተከታታይ ነጥብ የጣልንባቸው ጨዋታዎች ሁሉ ጥሩ ተንቀሳቅሰን ነበር። ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች ማግኘት የሚገባንን ነጥብ እንዳናገኝ መሆኑ በጣም ጫና ውስጥ ከቶን ነበር። ዛሬ ማሸነፍ እንዳለብን ተነጋግረን ያሉብንን ድክመቶች አስተካክለን በከፍተኛ የመጫወት ፍላጎት ለጨዋታው ተዘጋጅተን ነበር የመጣነው። ፈጣሪ ይመስገን የምንፈልገውን ነጥብ አስመዝግበናል። ዛሬ ማሸነፋችን ከዚህ በኃላ ላሉብን ጨዋታዎች የበለጠ እንድንሰራ ሞራል ይሆነናል።

“በሰውነቴ አጭር ቀጭን ብሆንም ፈጣሪ ጥንካሬውን እና ብስለቱን ሰጥቶኛል። መሐል ሜዳው በጣም ፍትጊያ የሚበዛበት ቢሆንም በጥንቃቄ ራሴን ጠብቄ ኳሱ ላይ ብቻ ትኩረት አድርጌ እጫወታለው። ወደ ፊትም በየ ጊዜው ራሴን እያሻሻልኩ ከዚህ የተሻለ የመጫወት አቅሜን ለማሳየት እሞክራለው።

“በብሔራዊ ቡድን የመጫወት ፍላጎት አለኝ። አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ጠርቶኝ ሠላሳ ስድስት ውስጥ አካቶኝ ነበር። ወደ ዋናው ስብሰብ ያላካተተኝን ምክንያት ነግሮኝ በሂደት እንደሚጠራኝ ቢነግረኝም እርሱ ከብሔራዊ ቡድን ለቋል። አሰልጣኝ ውበቱ ደውሎልኝ አንዳንድ መስራት ያለብኝ ነገሮችን ነግሮኛል እኔም ጠንክሬ እየሰራው ነው። ጥሩ ነገር ይዤ እመጣለው ብዬ አስባለው።

” የጅማ አባቡና የመፍረስ አደጋ ውስጥ ገብቶ እንደነበረ ስሰማ በጣም ነው ያዘንኩት። አባቡና ያሳደገኝ ክለብ እና በጣም የምወደው ደስ የሚለኝ ቡድን ነው። በዚህ ሰዓት ይህ ቡድን እንደዚህ መሆኑ በጣም ተሰምቶኛል። የበፊቱ አባቡና ይመለሳል ብዬ ተስፋ አደርጋለው። ወደ ፊት ወደ ጅማ ሄጄ የምጫወትበት መንስኤም ቢፈጠር ደስ ይለኛል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ