ቅድመ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮጵያ ቡና

የስድስተኛ ሳምንት መክፈቻ የሆነውን የሸገር ደርቢ የተመለከተው ዳሰሳችንን እነሆ።

የመዲናይቱ ሁለት ክለቦች ከድል መልስ የሚገናኙበት ተጠባቂ ጨዋታ ነገ ረፋድ ላይ ይከናወናል። በእርግጥ ባለፉት ዓመታት የሸገር ደርቢ በሜዳ ላይ የታሰበውን ያህል ፉክክር ሳያሳየን የጎል ድርቅም እየመታው ሲጠናቀቅ ቆይቷል። ይህ መሆኑ ተጠባቂነቱን ባይቀንሰውም ጓጉቶ ለሚጠብቀው የስፖርት ቤተሰብ የሚጠበቀውን ያህል አዝናኝ አለመሆኑ ቅሬታን የሚፈጥር ነው። ለዚህ እንደአንድ ምክንያትነት የሚነሳው የሜዳ ላይ ጡዘቱ ወደ ደጋፊዎች ግጭት እንዳያመራ የመሰጋቱ ነገር ዘንድሮ በኮቪድ 19 ምክንያት ጨዋታዎች በዝግ በመካሄዳቸው የማይኖር በመሆኑ ጨዋታው ከፍ ያለ ፉክክር እንዲኖረው በር ሊከፍት እንደሚችል ይገመታል። የቡድኖቹ ተጨዋቾችም ቀለል ባለ ጫና ውስጥ ሆነው ሲገናኙ የተሻለ ብቃታቸውን አውጥተው ለመጨወት ዕድል እንደሚያገኙም ይታሰባል።

ከሰባት ቀናት በኋላ ወደ ጨዋታ የሚመለሰው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሦስት ተከታታይ ድሎችን በማሳካት መልካም አቋም ላይ ይገኛል። ከማሸነፍ በዘለለ በየጨዋታዎቹ ያስቆጠራቸው ግቦች ቁጥር ከፍ ማለትም ከእንደነገው ዓይነት ጨዋታ በፊት የቡድኑን በራስ መተማመን ከፍ ለማድረግ የሚረዳ ሌላው በጎ ነጥብ ነው። ወደ ቀደመ የቀጥተኛነት አጨዋወቱ የማዘንበል ባህሪ እየታየበት ያለው ጊዮርጊስ ከተከላካይ ጀርባ የሚገኙ ክፍተቶችን በአግባቡ በመጠቀም ጥንካሬውን ማሳየት ችሏል። ነባሮቹም ሆኑ አዳዲሶቹ ፈራሚዎች ግብ በማስቆጠር እና ጨዋታ ለዋጭ ተፅዕኖዎችን በመፍጠር እያሳዩ ያሉት ብቃት ቡድኑ አማራጮች እንዲሰፉለት ጨዋታው ቢከብደው እንኳን በተጫዋቾች የግል ብቃት የሚገኙ ግቦችን ለማስቆጠር የሚረዳው ጉዳይ ነው። በተለይ ኢትዮጵያ ቡና ከኃላ መስመር ላይ ከሚሰራው ተደጋጋሚ ስህተት አንፃር የፈረሰኞቹ ቀጥተኝነት እና ፊት ላይ ያሉ ተሰላፊዎቻቸው ፍጥነት ተጠቃሚ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ይገመታል። ቡድኑ መሀል ሜዳ ላይ ኳስን የማቆየት ሀሳብ ካለው ግን የተሻለ ውህደት ባለው ተጋጣሚው መፈተኑ የሚቀር አይመስልም።

ኢትዮጵያ ቡና እንደተጋጣሚው ረዘም ያለ የማገገሚያ ጊዜ ባይኖረውም ከኋላ ተነስቶ ያሸነፈበት የሰበታው ጨዋታ ትዝታ ትኩስ መሆኑ የቡድኑ ጉልበት ላይ የሚጨምርለት አዕምሯዊ ጥንካሬ ይኖራል። የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን አብዝተው የሚፈልጉት ቡናማዎቹ እንደ ሰበታው ጨዋታ ታታሪነት የታከለበት እና የፊት መስመር ተሰላፊዎች እገዛ ያልተለየው እንቅስቃሴ የመሀል ሜዳውን ጦርነት ለማሸነፍ ትልቅ እገዛ ያደርግላቸዋል። እንደዊሊያም ሰለሞን እና ሬድዋን ናስር ዓይነት ወጣት ተጫዋቾቻቸው ጭምር ቡድኑ ለሚፈልገው አካሄድ በጨዋታ ጭምር ተፈትነው ለደርቢው መድረሳቸውም ለቡድኑ ተጨማሪ ኃይል ይሆነዋል። ምንም እንኳን ከተጋጣሚው በራሱ ሜዳ ከፍ ያለ ጫና ሊደርስበት እንደሚችል ቢገመትም ያንን የሚያልፍበት ጥሩ ዕቅድ ከኖረው የጊዮርጊስን የአማካይ ክፍል ተጋፍጦ የመጨረሻ ኳሶችን ለማድረስ የተሻለ ዕድል ይኖረዋል። ይህን ለማድረግ ግን ተደጋጋሚ ለውጦች የተደረጉበት የቡድኑ የተከላካይ አማካይ ተሰላፊ ሚና ከፍ ያለ ነው። ፊት መስመር ላይ ያሉት የቡድኑ ተሰላፊዎችም እንዲሁ ከግብ አስቆጣሪነቱ ሳይቦዝኑ ለጨዋታው መድረሳቸው ለአሰልጣኝ ካሳዬ ቡድን ጥንካሬን የሚያላብስ ነው። ቡድኑ ከኋላ ያለከፍተኛ ጫና ሲሰራቸው እና ዋጋ ሲያስከፍሉት የሰነበቱት ስህተቶች ግን ነገ ከበድ ባለ ጫና ዳግም የመፈተሻቸው ነገር ስጋት የሚጭር ይሆናል።

በቡድኖቹ የተሻለ የማጥቃት ተሳትፎ ያላቸው ተከላካዮች ሄኖክ አዱኛ እና ኃይሌ ገብረትንሳይ ወደ ፊት ለመሄድ ከተቃራኒ ቡድን የመስመር አጥቂዎች የሚገጥማቸው ፈተና ፣ ታፈሰ ሰለሞንን ከሙላለም መስፍን ያሚያጋፍጡ ቅፅበቶች ፣ የጊዮርጊሶቹ አቤል ያለው እና አዲስ ግደይ ከቡና የተከላካይ መስመር ፊት እና ኃላ ያሉ ቦታዎች ላይ የሚኖራቸው ተፅዕኖ ፣ የቡና መስመር አጥቂዎች በጊዮርጊስ መሀል እና መስመር ተከላካዮች መሀል ለመግባት የሚያደርጉት ጥረት እንዲሁም የጌታነህ ከበደ እና የአቡበከር ናስር ከተከላካይ መስመር ጋር የሚኖራቸውን ግብግብ በነገው ሸገር ደርቢ የምንጠብቃቸው የሜዳ ላይ ፍልሚያዎች ይሆናሉ።

ጉዳት እና ተያያዥ ጉዳዮችን የተመለከቱ የቡድን ዜናዎችን ለማካተት ያደረግነው ጥረት በሁለቱም ክለቦች በኩል መረጃ ባለማግኘታችን አልተሳካም።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 40 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 18 ጨዋታ ሲያሸንፍ፤ ኢትዮጵያ ቡና 6 ድል አሳክቷል። በ16 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

– የሸገር ደርቢ ምንም እንኳ አሁን አሁን ያለ ግብ የሚጠናቀቅባቸው ጨዋታዎች በርከት ቢሉም ባለፉት 40 ግንኙነቶች 73 ጎሎች ተቆጥረዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ 49፤ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 24 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)

ፓትሪክ ማታሲ

ሄኖክ አዱኛ – ምንተስኖት አዳነ – አስቻለው ታመነ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ

ሀይደር ሸረፋ – ሙሉዓለም መስፍን

አቤል ያለው – ሮቢን ንጋላንዴ – አዲስ ግደይ

ጌታነህ ከበደ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

ተክለማሪያም ሻንቆ

ኃይሌ ገብረትንሳይ – ወንድሜነህ ደረጄ – አበበ ጥላሁን – አሥራት ቱንጆ

ታፈሰ ሰለሞን – ረመዳን ናስር – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን

አቤል ከበደ – ሀብታሙ ታደሰ – አቡበከር ናስር


© ሶከር ኢትዮጵያ