ሪፖርት | የተነቃቃው ሲዳማ ቡና የዓመቱን ሁለተኛ ድል አስመዝግቧል

የቤትኪንግ የኢትዮጰያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ቀን ውሎ ከሰዓት ሲቀጥል ድሬዳዋን የገጠመው ሲዳማ ቡና 3-1 ማሸነፍ ችሏል።

በሲዳማ በኩል በፋሲል ከነማ ከተሸነፈው ስብስብ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ሰንዴይ ሙቱኩ፣ ማማዱ ሲዲቤ እና ተመሽገን በጅሮንድ በላውረንስ ኤድዋርድ፣ እሱባለው ሙሉጌታ እና አማኑኤል እንዳለን ቦታ ተተክተው ጨዋታውን ሲጀምሩ ድሬዳዋ ከተማም በባህር ዳር ከተማ ከተሸነፈበት ጨዋታ በተመሳሳይ ሦስት ለውጦች አድርጎ ምንያምር ጴጥሮስ፣ ሱራፌል ጌታቸው እና ጁንያስ ናንጄቦ በያሬድ ዘውድነህ ፣ ሪችሞን ኦዶንጎ እና ፍሬዘር ካሳ ምትክ ተሰልፈዋል።

ጨዋታው በድሬዳዋ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን ገና አንድ ደቂቃ ሳይሞላ ሙኅዲን ሙሳ የተጣለለትን ኳስ ተቆጣጥሮ በመግባት የሞከረው ኳስ የጎሉን ቋሚ ገጭቶ ወጥቷል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ሰንዴይ ሙቱኩ ወደፊት ለማቀበል የሞከረውን ኳስ ሙኅዲን አቋርጦ ወደ ሳጥን ይዞ በመግባት ገና በጊዜ ድሬዳዋን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ቀዝቀዝ ብለው የጀመሩት ሲዳማዎች ከጎሉ በኋላ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ቶሎ ቶሎ ወደ ድሬዳዋ የጎል ክልል በመድረስ ጫና መፍጠር ችለዋል። በዚህም በ16ኛው ደቂቃ ማማዱ ሲዲቤ ያመቻቸለትን ኳስ በጥሩ አቋቋም ሆኖ ሲጠብቅ የነበረው ሀብታሙ ገዛኸኝ ወደ ጎልነት ቀይሮ ቡድኑን አ አድርጓል።

ከአቻነት ጎሉም በኋላ በነበራቸው ተነሳሽነት የቀጠሉት ሲዳማዎች ጥሩ ጥሩ የጎል አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል። በተለይ በ24ኛው ደቂቃ ያስር ሙገርዋ አክርሮ መትቶ ፍሬው ያወጣበት እና የማዕዘን ምቱ ሲሻማ ሰንዴይ ሙቱኩ በግንባር ገጭቶ ወደ ውጪ የወጣበት ለጎል እጅግ ያቃረባቸው አጋጣሚ ነበር። ጨዋታው በዚህ ቀጥሎ ብዙም ሳይቆይ ግማሽ ጨረቃ አካባቢ በ28ኛው ደቂቃ የተገኘውን የቅጣት ምት ማማዱ ሲዲቤ በግሩም አመታት ማስቆጠር ችሏል።

ሁለተኛው አጋማሽ ድሬዎች ኳስን ተቆጣጥረው ቢጫወቱም ለሲዳማ የኋላ ክፍል ፈታኝ የሆነ ጫና መፍጠር የተሳናቸው ሲሆን በተቃራኒው ሲዳማዎች በመልሶ ማጥቃት ፍሬው ጌታሁን አዳናቸው እንጂ በርካታ ጎል ሊሆኑ የሚችሉ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። በተለይም ሀብታሙ ሳጥን ውስጥ ከሲዲቤ የተቀበለውን ኳስ አክርሮ መትቶ ፍሬው በግሩም ቅልጥፍና ያወጣበት፣ አማኑኤል እንዳለ አፈትልኮ ወጥቶ ወደ ግብ መትቶ ሲመልሰው መለሰበት እና በድጋሚ መትቶ አሁንም ግብ ጠባቂው ያዳነበት እንዲሁም ሀብታሙ ከመስመር ወደ ውስጥ ይዞ ገብቶ የመታውን ግብ ጠባቂው የመለሰበት ሙከራዎች ድሬዳዋን በሰፊ ልዩነት ከመሸነፍ የታደጉ ነበሩ።

ወደ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ድሬዎች የማጥቃት ባህርይ ያላቸው ተጫዋቾችን በማብዛት አቻ ለመሆን ቢያስቡም አስደንጋጭ የሚባል ሙከራ ያላደረጉ ሲሆን ይልቁንም በዛሬው ጨዋታ ደምቆ የታየው ማማዱ ሲዲቤ በ83ኛው ደቂቃ ከዳዊት ተፈራ የተቀበለውን ኳስ ወደ ፊት በመግፋት ጠንከር ባለ ምት ወደ ግብነት ቀይሮ የሲዳማን መሪነት አስፍቷል። ጨዋታውም በቀሪ ደቂቃዎች ተጨማሪ ጎል ሳይስተናገድበት በሲዳማ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የድሬዳዋ ከተማው ተከላካይ በረከት ሳሙኤል በገጠመው ጉዳት ተቀይሮ ወጥቷል። 


© ሶከር ኢትዮጵያ