“ውጤቱ በጣም ያስፈልገን ነበር ” – ፀጋዬ ብርሀኑ

ወላይታ ድቻ ከተከታታይ ስድስት ጨዋታዎች በኃላ ወደ አሸናፊነቱ እንዲመለስ እና ለጊዜውም ቢሆን ከጫና እንዲወጣ ያስቻሉ ሁለት ወሳኝ ጎሎች ያስቆጠረው ፀጋዬ ብርሀኑ ይናገራል።

ከወላይታ ዞን ገጠራማ አካባቢ ተመልምሎ እስከ ዋናው ቡድን ደረስ መጫወት የቻለው ፀጋዬ ያለፉትን አምስት ዓመታት በወላይታ ድቻ ቢያሳልፍም ተደጋጋሚ ጉዳቶች እና በተለያዩ ቦታዎች ላይ መሰለፉ በሚፈለገው ደረጃ እድገት እንዳያሳይ አድርገውት ቆይተዋል። ዘንድሮ ግን ምንም እንኳ ቡድኑ ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ ባይገኝም በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ያለውን አቅም በሚገባ እያሳየ ይገኛል። ከኳስ ውጪ ያለው እንቅስቃሴ፣ ቡድኑ በሚጠቃበት ወቅት ለመከላከል የሚያሳየው ፈቃደኝነት እና የጨዋታ ፍላጎቱ የፀጋዬ መገለጫዎች ናቸው። ጎል የማስቆጠር አቅሙንም በማሻሻል አራት ጎሎችን በዘንድሮው የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ላይ አስቆጥሯል።

በዛሬው ዕለት ለወላይታ ድቻ እጅግ አስፈላጊ በሆነው ጨዋታ ከስድስት ተከታታይ ውጤት አልባ ጉዞ በኃላ ኢትዮጵያ ቡናን ከመመራት ተነስቶ እንዲያሸንፉ ያስቻሉ ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር የእሱ ሚና የጎላ ነበር። በአንድ ወቅት አሰልጣኝ አሸነፊ በቀለ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ በነበሩበት ወቅት ለሴካፋ ውድድር ለብሔራዊ ቡድን ጥሪ ተደርጎለት የነበረው ፀጋዬ ከዛሬው ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ አሁን ስለሚገኝበት ወቅታዊ አቋም እና ተያያዥ ጉዳዮች አንስተንለት ተከታዩን ሀሳብ ለድረ ገፃችን ገልፂል።

” የዛሬው ጨዋታ ያደረግነው በጣም በጫና ውስጥ ሆነን ነበር፤ ይህ የሆነው ካለን ነጥብ አንፃር ነው። በዚህ ሒደት ውስጥ ጎል ተቆጥሮብን ነበር። ተጭነን መጫወት እንዳለብን ተነጋግረን ነበር ከዕረፍት በኃላ የገባነው፤ ውጤቱም ተሳክቶልናል። የዛሬው ሦስት ነጥብ ለእኛ ለቀጣዩ ጨዋታ ስንቅ የሚሆነን በመሆኑ ውጤቱ በጣም ያስፈልገን ነበር። በዚህም በጣም ደስ ብሎኛል።

“ያው የተለያየ ቦታ መጫወቴ በአንድ ነገር ላይ ስኬታማ እንዳልሆን አድርጎኛል። በዚህ ዓመት መጀመርያ በነበረው አሰልጣኝ የመስመር አጥቂ ሆኜ እጫወት ነበር። አሁን ደግሞ ወደ ጅማ ከመጣን በኃላ ሀሰተኛ አጥቂ ሆኜ እየተጫወትኩ ነው። ዛሬ መጀመርያ አጥቂ ነበርኩ። ያው አሰልጣኞች የሚሰጡኝን ታክቲክ መተግበር ግዴታዬ ነው። የምችለውን ለማድረግ እየጣርኩ ነው።

“የተፈጥሮ ነገር ይሆናል አንዳንዴ ሜዳ ውስጥ ብዙ ነገር አድርገህ በሚዲያም ሊሆን ይችላል በብሔራዊ ቡድን ምርጫ ውስጥ ዕይታ ላልገባ እችላለሁ። ከዚህ በኃላ ግን በሚገባ ራሴን እያሳየሁ እመጣለው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ