“ገና ብዙ ይቀረኛል፤ ያሉብኝን ክፍተቶች አሻሽዬ የተሻለ መሆን እፈልጋለው” – አብዱልከሪም ወርቁ

ከፍተኛ ዕድገት በማሳየት መልካም የውድድር ዓመት እያሳለፈ የሚገኘው የወልቂጤው አማካይ አብዱልከሪም ወርቁ ስለ አስደናቂ አቋሙ ልጠይቀው ወደን አናግረነዋል።

የወደፊት ተስፋ የሚጣልበት ወጣት ስለመሆኑ ሶከር ኢትዮጵያ ሁሌም ተስፈኛ ወጣቶችን በምታነቃቃበት ቋሚ አምዷ ስለዚህ ባለተስዕጦ ተጫዋች ማስነበቧ ይታወቃል። ይህ ወጣት አዲስ አበባ ልደታ ሠፈር ተወልዶ በማደግ በኒያላ እና ኢትዮጵያ መድን የታዳጊ የእግርኳስ ህይቱን በመግፋት በአሁኑ ወቅት በሠራተኞቹ ቤት ወሳኝ ተጫዋች መሆኑን እያስመለከረ ይገኛል። ከኳስ ውጭ የሚያደርገው አስገራሚ እንቅስቃሴ እንዳለ ሆኖ ኳስ እግሩ ሲገባ በሰውነቱ እንቅስቃሴ ተጫዋቾችን የሚያልፍበት መንገድ ትኩረትን የሚስብ ነው። ከዚህ ቀደም አሉብኝ ያላቸውን ድክመቶች አርሞ በወጥ አቋም ወደ ውድድር የገባው ወጣቱ አማካይ አብዱልከሪም ወርቁ ስለ ወቅታዊ አቋሙ ለሶከር ኢትዮጵያ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥቷል።

” ከሞላ ጎደል ዓምና ከነበረብኝ ድክመት ተነስቼ ዘንድሮ ጥሩ ነገር ለማድረግ የተለየ ዝግጅት ሳደርግ ቆይቻለሁ። አሁን ያለሁበት ሁኔታ ጥሩ ቢሆንም ከዚህ በላይ መሥራት እፈልጋለው። የኳስ ክህሎቴ እንዳለ ሆኖ የአቅም ችግር ነበረብኝ። ይህን አሰልጣኞቼ በተደጋጋሚ እንዳስተካክል ይነግሩኝ ነበር። “ኳስ ላይ ጥሩ ነህ፤ ጉልበት ጨምር” ይሉኝ ነበር። ለዚህም በኮሮና ወቅት ጉልበቴን የሚያዳብርልኝ ጠንካራ ሥራ ስሰራ ቆይቼ ነበር። ለዛም ነው ጫናዎችን በመቋቋም መንቀሳቀስ የቻልኩት።

” ከኳስ ውጭ እንቅስቃሴ አታደርግም። ይሄንም ማስተካከል አለብህ ስላሉኝ ነው ከኳስ ውጭ የነበረብኝን ድክመት አስተካክዬ የመጣሁት። ኮሮና ምክንያት ውድድሩ መሰረዙ ለኔ መሻሻል በጣም ጠቅሞኛል። በሰውነቴ ሚዛን አስቼ የማለፌ ምክንያት ከልጅነቴ ጀምሮ የነበረኝ ልምድ ነው። ያነው እያደገ መጥቶ አሁን ላይ ሜዳ ውስጥ እያሳየሁት ያለሁት።

“ገና ብዙ ይቀረኛል። ያሉብኝን ክፍተት አሻሽዬ የተሻለ ነገር መስራት እፈልጋለው። ብዙ ሰው ከጎኔ በመሆን ያበረታታኛል። ቤተሰቦቼም በጣም ነው የሚያግዙኝ ለዚህም በጣም ላመሰግናቸው እወዳለሁ።”


ከዚህ ቀደም በተስፈኞች አምዳችን ከአብዱልከሪም ወርቁ ጋር ያደረግነውኝ ቆይታ ከታች ያለውን ርዕስ በመጫን ያገኙታል።

“የሚያምንብህ አሰልጣኝ እና ክለብ ካገኘህ አቅምህን ማሳየቱ ቀላል ነው” ተስፈኛው አብዱልከሪም ወርቁ


© ሶከር ኢትዮጵያ