የአሰልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 2-1 ኢትዮጵያ ቡና

ወላይታ ድቻ ቡናን 2-1 ካሸነፈበት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ዘላለም ሺፈራው – ወላይታ ድቻ


ስለመጀመርያ አጋማሽ የተጫዋች ቅያሪ

” ቡና ኳስ መስርቶ እንደሚጫወት ይታወቃል። በመጀመርያ አጋማሽ በነበረን እንቅስቃሴም ከፍተኛ ጫና በመፍጠር ነበር ለመጠቀም የፈለግነው። ከዚህ ቀደም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ይዘነው የገባነው አጨዋወት ጥብቅ መከላከል ነበር። ያ ግን ቡና ላይ አይሰራም የሚል ሀሳብ ስለነበረን ጫና በማሳደር መጫወት ነው የፈለግነው። ለዛ ደግሞ የአጥቂ አማካዩ ሚና ጉልህ ነበር። ሆኖም የፈለግነውን ነገር ከኤልያስ አላገኘንም። ለዛ ነው ቶሎ ቅያሪ ያደረግነው።”

ስለ ፀጋዬ ብርሀኑ

” እንደ ቡድን በመጀመርያው 45 ፍፁም ተቀዛቅዘን ነበር። ያ መቀዛቀዝ ፀጋዬም ላይ ተፅእኖ ነበረው። በእረፍት ሰዓት የተነጋገርነውም ያንን ነበር። ከፍተኛ የሆነ የጨዋታ ፍላጎት እንደሚያስፈልገን ተነጋግረን ነው የተመለስነው። በዚህም ሒደት ፀጋዬ ከዚህ በፊት የሚታወቅበትን ነገር ነው ያሳየው። እንደ አጠቃላይ ቡድናችን ላይ የነበረው መነሳሳት ከፍ ያለ ነበር።”

አሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለመጀመርያ አጋማሽ አቀራረብ

” ድቻዎች ኳስን ቶሎ ቶሎ ለማስጣል ነበር የሚመጡት። ለዛ ደግሞ ፈጣን ምላሽ ያስፈልጋል። አንደኛ እነሱ ማፈን በፈለጉበት መንገድ እንዳያፍኑን ሜዳውን አስፍተን የመጫወቻ ሜዳ መፍጠር ነበረብን፤ በዚህ ጥሩ ነበርን። የቱ ጋር ሊያፍኑ እንደሚፈልጉም ገብቶን ስለነበር ሜዳውን ለጥጠን ተጫውተናል። ”

ጎሎች ስለተቆጠሩበት መንገድ

” ከኛ የአጨዋወት ባህርይ አንፃር እንዲህ አይነት ክፍተቶች ይፈጠራሉ። እንዲህ አይነት ክፍተት ሲፈጠር ተጋጣሚ እንዳይጠቀምበት ምን ማድረግ አለብን የሚለው ላይ የመስራት ጉዳይ ነው። ወደፊትም እንዲህ አይነት ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የማንገኝበትን መንገድ አጠናክረን እስካልሰራን ድረስ። የመጀመርያው ጎል የተቆጠረበት መንገድ የመገባበዝ ነበር። አበበ ተክለማርያምን ሲጠብቅ ተክለማርያም አበበን ይጠብቃል። በዚህ መሐል ነው የነሱ አጥቂ ተጠቃሚ የሆነው። እንዲህ አይነት ነገሮች በእግርኳስ የሚያጋጥሙ ናቸው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ