ሪፖርት | ዐፄዎቹ በጌታነህ ከበደ ብቸኛ ግብ ከተከታታይ አቻዎች በኋላ ወደ ድል ተመልሰዋል

የ25ኛ ሳምንት የመጀመርያ ቀን የምሽት ጨዋታ ከፍተኛ ንፋስ በቀላቀለ ዝናብ ታጅቦ በተደረገው ጨዋታ ፋሲል ከነማዎችን ባለ ድል ሲያደርግ ወልቂጤ ከተማዎች አሁን የአሸናፊነቱ መንገድ እንደጠፋቸው ቀጥለዋል።

በደርቢው ጨዋታ ነጥብ ከተጋራው ስብስብ ፋሲል ከነማዎች ባደረጓቸው አምስት ለውጦች ዮሐንስ ደርሶ፣ አምሳሉ ጥላሁን፣ ሽመክት ጉግሳ፣ ፍቃዱ አለሙ እና ጃቢር ሙሉን አስወጥተው በምትካቸው ሳማኪ ሚካኤል፣ ሀቢብ መሀመድ፣ ዮናታን ፍስሀ፣ አቤል እያዩ እና ቃልኪዳን ዘላለም በመተካት ወደ ሜዳ ሲገቡ በአንፃሩ ወልቂጤ ከተማዎች በባለፈው የጨዋታ ሳምንት ሽንፈት ያስተናገደውን ስብስብ ሳይለውጡ ለጨዋታው ቀርበዋል።

በዝናባማ አየር ታጅቦ በፌደራል ዳኛ ተካልኝ ለማ መሪነት በጀመረው የምሽቱ ጨዋታ ምንም እንኳን ሜዳው ላይ ይዘንብ የነበረው ዝናብ ቢቆምም ሜዳው ላይ በቋጠረው መጠነኛ ውሃ ምክንያት ኳሶችን መጥኖ ለማቅረብ እና ኳሶችን በሚፈልገው ልክ ለማሸራሸር ለሁለቱም ቡድኖች ሜዳው አዳጋች አድርጎባቸው ተስተውሏል።

በሚደረጉ ቅብብሎሽ አደጋ የሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎች ሳንመለከት የዘለቀው ጨዋታ የመጀመርያው ሙከራ እና ጎል አስራ አምስተኛው ደቂቃ ላይ አስመልክቶናል። በአንናፃራዊነት የተሻለ የነበሩት ፋሲል ከነማዎች ከጋቶች ፓኖም መነሻ አድርጎ ወደ ሳጥን ውስጥ ለቃልኪዳን የተላከው ኳስ በግብጠባቂው መሳይ አያኖ የጊዜው አጠባበቅ ስህተትን ተጠቅሞ ቃልኪዳን ለጌታነህ ከበደ አቀብሎት በጥሩ አጨራረስ ወደ ጎልነት የቀየራት አጋጣሚ ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች ፤ ይህችም ጎል ጌታነህ ከበደ ከስምንት ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ ያስቆጠራት የሊጉ ዘጠነኛ ጎሉ ሆና ተመዝግባለች።

ጥራት ያላቸው የጎል ሙከራ ለማድረግ የተቸገሩት ሰራተኞቹ አልፎ አልፎ በጥሩ ቅብብል መስመሮችን ተጠግተው ወደ ፊት በመሄድ አደጋ ለመፍጠር ቢያስቡም ጥረታቸው በሚፈለገው ልክ ፋሲሎችን ለመፈተን ብቁ አልነበሩም ፤ በ30ኛው ደቂቃ በጥሩ የኳስ ንኪኪ ተመስገን በጅሮንድ አግኝቶ በቀጥታ ወደ ጎል ቢመታውም ግብጠባቂ ሳማኪ ሚካኤል ወደ ውጭ ያወጣበት ኳስ ለወልቂጤዎች በአጋማሹ የተፈጠረ ብቸኛው ግልፅ የጎል ዕድል ነበር።

ከዕረፍት መልስ በ51ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጭ ሙሉዓለም መስፍን የግብ ጠባቂውን አቋቋም ተመልክቶ በግሩም ሁኔታ የመታውን ግብጠባቂው ሳማኪ ሚካኤል እንደምንም ተስቦ ወደ ውጭ ባወጣበት ኳስ የጀመረ ሲሆን በአጋማሹ ጅማሬ የነበራቸውን የማጥቃት ጥረት ማስቀጠል ያልቻሉት ወልቂጤዎች በ60ኛው ደቂቃ ጎል ለማስተናገድ ተቃርበው ነበር።

ጌታነህ ከበደ ከተሻጋሪ ኳስ የተቀበለውን ወደ ጎል ቢመታው በቀላሉ መቆጣጠር የሚችለውን ግብጠባቂው መሳይ አያኖ የሾለከችበትን ኳስ ቃልኪዳን ዘላለም ወደ ጎልነት ቀየረው ሲባል ወንድማገኝ ማዕረግ ወደ ውጭ አውጥቶት ቡድኑን በጨዋታው ማቆየት ችሏል።

85ኛው ደቂቃ ላይ በአንፃራዊነት የተሻለ ብልጫ የነበራቸው ሰራተኞቹ በሁለት አጋጣሚዎች ከእንቅስቃሴ ይልቅ በቆሙ ኳሶች አደጋ ሊፈጥሩ ቢችሉም በጨዋታ በንቃት ስህተት ሳይሰሩ የቆዮት የፋሲል ከነማ ተከላካዮች በቀላሉ ሊቆጣጠሯቸው ችለዋል። ይሀን ተከትሎ ጨዋታው በፋሲሎች የ1-0 አሸናፊነት መጠናቀቅ ችሏል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ በተሰጡ አስተያየቶች አሰልጣኝ ሙልጌታ ምህረት ከሞላው ጎደል እንቅስቃሴያቸው ጥሩ ቢሆንም የሚፈልጉትን ነገር ግን አለማግኘታቸውን ገልፀው ጎሉ አስኪቆጠርባቸው ድረስ በጥንቃቄ ጨዋታውን ለመቆጣጠር አለመቻላቸው ጠቅሰው ቡድኑ ያለበት የአጥቂ ችግር ስራቸውን እንዳከበደባቸው ተናግረዋል።አሰልጣኝ ውበቱ በበኩላቸው ጠንካራ ትግል እንደሚጠብቃቸው አውቀው ወደ ሜዳ እንደመጡና የሜዳውም ሁኔታ ተጨማሪ ፈተና እንደሆነባቸው ሲገልፁ ከዚህ ጨዋታ ወሳኙን ነጥብ በማግኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው በቀጣይ በጥሩ ደረጃ ለመጨረስ እንደሚሞክሩም ተናግረዋል።