ቅድመ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

የዘጠነኛውን ሳምንት የሦስተኛ ቀን ውሎ የረፋድ ጨዋታ የተመለከተው ዳሰሳችን እንዲህ ይነበባል። 

ከሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ የሚገናኙት ሁለቱ ቡድኖች መጠነኛ እፎይታ ሊሰጧቸው የሚችሉ ሦስት ነጥቦችን ለማግኘት እርስ በእርስ የሚፋለሙ ይሆናል። 

ከባድ የውድድር ዓመት እያሳለፈ የሚገኘው አዳማ ከተማ በእንቅስቃሴ ደረጃ መጠነኛ መሻሻል ቢያሳይም ያለበትን ሁኔታ ለማስተካከል ግን በቂ አልሆነም። ቡድኑ ከፋሲል ጋር በነበረው የመጨረሻ ጨዋታ በድፍረት የማጥቃት ሀሳብ ኖሮት ቢታይም በሰፊ ልዩነት መሸነፉ ግን አልቀረም። ቡድኑ ባለፉት ጨዋታዎች ላይ ከገጠሙት ቡድኖች በተለየ ደካማ የመከላከል አደረጃጀት ያለው ድሬዳዋ ከተማን የሚገጥም ከመሆኑ አንፃር በርካታ የጎል ዕድሎችን የመፍጠርያ አጋጣሚዎች እንደሚያገኝ ይገመታል። በተለይም አምበሉ የኋላሸት ፍቃዱ ከኳስ ውጪ በሚያደርገው እንቅስቃሴ የሚፈጥረውን ክፍተት በአግባቡ መጠቀም ከቻሉ ከጨዋታው ድል ይዘው ሊወጡ ይችላሉ። ሆኖም ከዚህ ቀደም የሚያገኛቸውን ጥቂት እድሎች በሚያባክኑበት ቁመና ላይ ሆነው ላለመቅረብ የአጨራረስ ድክመታቸውን ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል። ለዚህም ከጉዳት ተመልሰው በሚፈለገው የአካል ብቃት ደረጃ ላይ ያልነበሩት እንደ አብዲሳ ጀማል ያሉ አጥቂዎች ጎል ፊት ያላቸውን አቋም ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል።

ከወራጅ ቀጠናው አፋፍ ላይ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ በተከታታይ ሁለት ጨዋታ አሸንፎ መነሳሳት ቢታይበትም ባለፉት ሦሰት ጨዋታዎች ሽንፈት ማስተናገዱ እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ከባድ የውድድር ዘመን እንዲያሳልፍ እያስገደደው ይገኛል። የማጥቃትም ሆነ የመከላከል እንቅስቃሴው እንደቡድን የተደራጀ ከመሆን ይልቅ በተጫዋቾች የተናጠል ብቃት ላይ የተንጠለጠለ የሆነው የፍስሐ ጥዑመ ልሳን ቡድን ከመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች በተለየ በሀዲያው ጨዋታ የያዘውን የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ወደ ግብ ዕድሎች መቀየር ተስኖት መታየቱ ለነገውም ጨዋታ ስጋት ሊሆንበት ይችላል። በዚህ በኩል ለተከላካይ መስመሩ ሽፋን በመስጠትም ሆነ የተሳኩ ጥቃቶችን በማስጀመሩ ረገድ ተጋጣሚው ያለበት ድክመት ለድሬ ክፍተቶችን ሊያስገኝም ይችላል።

በጉዳት እና የተለያዩ ምክንያቶች ወጥ የተከላካይ መስመር ጥምረት ያላስመለከተን ድሬዳዋ ይህን በሚያሳብቅ መልኩ በተከታታይ ጨዋታዎች ድክመቶቹን ያጎሉ ጎሎች ተቆጥረውበታል። በነገው ጨዋታ በታታሪነት የሚጫወቱት የአዳማ አጥቂዎችን የሚቆጣጠሩበት መንገድም ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ነው።

በብርቱካናማዎቹ በኩል በረከት ሳሙኤል፣ ቢኒያም ጥዑመልሳን እና ሄኖክ ኢሳይያስ ከጉዳት ቢያገግሙም ለነገ ጨዋታ እንደማይደርሱ ሰምተናል። 

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ክለቦች በሊጉ 16 ጊዜ ተገናኝተው አዳማ ከተማ ስምንት ጨዋታዎችን በድል ሲያጠናቅቅ ድሬዳዋ አምስቱን አሸንፏል ፤ 3 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። አዳማ 17 ፣ ድሬዳዋ 12 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ (4-2-3-1)

ዳንኤል ተሾመ

አምሳሉ መንገሻ – ደስታ ጊቻሞ – ትዕግስቱ አበራ – እዮብ ማቲያስ

ሙጃይድ መሐመድ – ደሳለኝ ደባሽ

ፍሰሀ ቶማስ – በቃሉ ገነነ – የኋላእሸት ፍቃዱ

አብዲሳ ጀማል

ድሬዳዋ ከተማ (4-1-3-2)

ፍሬው ጌታሁን

ምንያምር ጴጥሮስ – ፍቃዱ ደነቀ – ፍሬዘር ካሣ – ዘነበ ከበደ

ዳንኤል ደምሴ

ሱራፌል ጌታቸው – ኤልያስ ማሞ – አስቻለው ግርማ

ኢታሙና ኬሙይኔ – ሪችሞንድ ኦዶንጎ


© ሶከር ኢትዮጵያ