ቅድመ ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

የሳምንቱ እና የሊጉ የጅማ ቆይታ መቋጫ የሆነውን ጨዋታ እንዲህ ተመልክተናዋል። ከ11 ቀናት በኋላ ወደ ሜዳ የሚመለሱት ፋሲል ከነማዎች ቀድመዋቸው ከተጫወቱት ተከታዮቻቸው ይበልጥ ለማራቅ ከነገው ጨዋታ የሚገኙ ነጥቦች ያስፈልጓቸዋል። የአዲስ አበባ የመጨረሻ ጨዋታቸውን ጨምሮ በጅማ ቆይታቸው አራት ተከታታይ ድሎችን ያስመዘገቡት ፋሲል ከነማዎች መረባቸውንም ሳያስደፍሩ እየወጡ ነው። በተቃራኒው በየጨዋታው ግብ እያስቆጠረ በሚገኘው አጥቂያቸው ሙጂብ ቃሲም ብቃት ታጅበው ግስጋሴያቸውን ቀጥለዋል። ቡድኑ በእዚህ ጥሩ ሂደት ላይ ሳለ ረዘም ያለ የዕርፍት ጊዜ ውስጥ መግባቱ ከአካሄዱ ካላቀዘቀዘው በቀር ከነገ ተጋጣሚው ወቅታዊ አቋም አንፃር የማሸነፍ ግምቱን ይወስዳል። አሁን ላይ የተቀረፈ የሚመስለው ፋሲል በአንዳንድ ጨዋታዎች መሀል ይታይበት የነበረው የትኩረት ማጣት ችግር ከተከሰተ ግን እንደ ሙኸዲን ሙሳ ዓይነት ስህተትን በአግባቡ ለሚጠቀሙ አጥቂዎች ሊጋለጥ ይችላል። ከዚህ አንፃር አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ቡድናቸው ለተጋጣሚው የሚሰጠው ግምት የተፋለሰ እንዳይሆን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ወሳኙ አማካይ ሱራፌል ዳኛቸው በአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት ሰዒድ ሁሴን ደግሞ በጉዳት ጨዋታው የሚያልፋቸው የአፄዎቹ ተጫዋቾች ናቸው። ከሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ አዳማን በተዋጣለት መንገድ አሸንፎ የነበረው ድሬዳዋ በወልቂጤ ሽንፈት ዳግም ደካማ ጎኖቹ ጎልተው ወጥተዋል። በተለይም የኋላ መስመሩ የግል እና የዲፓርትመንት ስህተቶች መበራከት ነገ በግል ጥረቱ ጭምር ዕድሎችን ለሚጠቀመው ሙጂብ ቃሲም በር እንዳይከፍቱ ያስጋዋል። አሰልጣኝ ፍሰሀ ጥዑመልሳን በቦታው ሦስት ዋነኛ ተጫዋቾቻቸው በጉዳት ባለመኖራቸው ክፍተቱን በተሻለ ቅያሪ የማስተካከል ዕድል የሌላቸው መሆኑ ችግሩን ያባብሰዋል። ቡድኑ ነገ ጥንቃቄ አዘል አቀራረብን ይዞ እንደሚቀርብ ሲጠበቅ መሀል ላይ የዳንኤል ደምሴ እና አስጨናቂ ሉቃስ ጥምረት በድጋሚ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል። በግሉ ጥሩ የግብ ማስቆጠር ሂደት ውስጥ የሚገኘው ሙኸዲን ሙሳ በሊጉ ጥቂት ግብ በማስተናገድ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ፋሲል ጋር የሚያደርገው ፍልሚያ ተጠባቂ ሲሆን ጁኒያስ ናንጄቦ በአሰላለፍ ውስጥ ከተካተተ ፍጥነቱን ተጠቅሞ የፋሲልን የኋላ ክፍል ሊፈትን ቢችልም ከሰሞኑ የተሻለ የአጨራረስ ብቃት ላይ ሊሆን የግድ ይለዋል። በረከት ሳሙኤል ፣ ፍቃዱ ደነቀ ፣ ያሬድ ዘውድነህ እና ቢኒያም ጥኡመልሳን አሁንም ጉዳት ላይ የሚገኙ ሲሆን ሄኖክ ኢሳይያስ ደግሞ ከጉዳት መልስ ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል። የእርስ በእርስ ግንኙነት – በሊጉ እስካሁን ስድስት ጊዜ ተገናኝተዋል። ፋሲል ከነማ ሁለት ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላይ ሲሆን አንድ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ አሸንፏል። በቀሪዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። – በተገናኙባቸው 6 የሊግ ጨዋታዎች ስድስት ጎሎች ብቻ የተቆጠሩ ሲሆን ፋሲል ከነማ አራት ፤ ድሬዳዋ ከተማ ሁለት ጎሎች አስቆጥረዋል። ግምታዊ አሰላለፍ ፋሲል ከነማ (4-2-3-1) ሚኬል ሳማኬ እንየው ካሳሁን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን ይሁን እንዳሻው – ሀብታሙ ተከስተ ሳሙኤል ዮሐንስ – በዛብህ መለዮ – ሽመክት ጉግሳ ሙጂብ ቃሲም ድሬዳዋ ከተማ (4-1-3-2) ፍሬው ጌታሁን ምንያምር ጴጥሮስ – ያሬድ ዘውድነህ – ኩዌኩ አንዶህ – ዘነበ ከበደ ዳንኤል ደምሴ – አስጨናቂ ሉቃስ ጁኒያስ ናንጄቦ – ኤልያስ ማሞ – አስቻለው ግርማ ሙኸዲን ሙሳ