ረዳት ዳኛው ለሁለት ወራት ታገዱ

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጅማ ላይ በተደረገ ጨዋታ የአፈፃፀም ግድፈት አሳይተዋል የተባሉት ረዳት ዳኛ ለሁለት ወራት ታግደዋል።

በዘጠነኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሰበታ ከተማ ከሀድያ ሆሳዕና ባደረጉት ጨዋታ 87ኛው ደቂቃ ላይ ዱላ ሙላቱ በቀኝ የሜዳው ክፍል ከሰበታው ተከላካይ መሳይ ጳውሎስ ቀድሞ ኳስ ለማግኘት በሚሮጥበት ወቅት መውደቁን ተከትሎ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛው ትግል ግዛው ተገቢ ያልሆነ የፍፁም ቅጣት ምት እንዲሰጥ አድርገዋል በሚል የዕለቱ የጨዋታ ታዛቢ ይድነቃቸው ዘውገ ያቀረቡትን ሪፖርት የመረመረው የዳኞች ብሔራዊ ኮሚቴ ረዳት ዳኛውን ለሁለት ወር ማገዱን ሰምተናል። የውሳኔ ደብዳቤም ነገ ይፋ ይሆናል።

በሌላ ዜና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው በሞሪታንያ አስተናጋጅነት የሚካሄደውን የ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫን ለመዳኘት ከጅማ ወደ ውድድሩ ስፍራ ማቅናታቸውን ሰምተናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ