የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 2-0 ድሬዳዋ ከተማ

ከ11ኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች ለሱፐር ስፖርት ኃሳባቸውን እንዲህ አካፍለዋል።

አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ

በመጀመሪያው አጋማሽ ቡድኑ ከኋላው ስለተወው ክፍተት

በመሰረቱ የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ጫና ለማድረግ ተሞክሯል። ግን ጫናው አዎንታዊ አልነበረም። ምክንያቱም እነ እነየው እና እነ በረከት ለቀው በሚሄዱበት ቦታ ሁሌም ክፍተት አለ። ያንን የመሸፈን ነገር ላይ ስህተት ነበር። ዕረፍት ላይ ብዙ ነገር ለመነጋገር ያተኮርነው እዛ ላይ ነበር። ጎል ስለተቻኮልክ አደጋ ነው። ስለዚህ ለመቆጣጠር ታክቲካሊ ቦታችንን ጠብቀን የሚሆነውን ነገር ለማድረግ መጣር ነው። ምክንያቱም ውጤቱ እጅግ እጅግ ያስፈልገን ነበር። እና የተጫዋቾቼም ፍላጎት እዛ ድረስ ነው። ስለዚህ በዚህ መካከል የተፈጠሩ ስህተቶች ናቸው። አጠቃላይ ሁኔታው ጥሩ ነው።

ስለቡድኑ የአደራደር ምርጫ

4-1-4-1 ሲሆን ሙጂብ ጀርባ ላይ የሚያግዘው መበራከት አለበት ፤ እሱን ነው ያረግነው። በኋላ ግን ወደ 4-2-3-1 ብዙ ጊዜ የለመድነው ጋር መሄድ ችለናል። በሁለቱም ቢሆን በቦታው ላይ ያሉ ተጫዋቾች ምን ያህል ስኬታማ ሆነዋል የሚለውን ነው እያረምን መሄድ ያለብን። በአጠቃላይ ግን ውጤቱን ስለምንፈልገው ለማጥቃት ብዙ ጥረት አድርገናል። ደህና ነው ብዬ ነው የማስበው።

አሰልጣኝ ፍሰሐ ጥዑመልሳን – ድሬዳዋ ከተማ

ቡድኑ ጨዋታው ሲጀመር የተገኙ ዕድሎችን ስላለመጠቀሙ

ሁልጊዜም እንግዲህ መጀመሪያ ላይ የምንስታቸው ኳሶች ዋጋ ያስከፍሉናል። 45ቱን ደቂቃ ጨርሰን ብንወጣ ኖሮ እዛች ሰዓት ላይ የነበረች ጥንቃቄ ፤ ያቺ ኳስ ገባች ከዛ የመበታተኑ ነገር መጣ።

ስለመስመር ተጨዋቾች አፈፃፀም

የተቻላቸውን ሞክረዋል። ግን ያው መጀመሪያ ላይ የነበረውን ጥንቃቄ መጨረሻዋ ሰዓት ላይ ብናረገው ኖሮ ምንአልባት ውጤቱ ለውጥ ሊኖረው ይችል ነበር። 1-0 ከወጣን በኃላ በሚቀጥለውም ያለው ነገር ያው በስህተት ገባብን። አንግል ገጭታ ስትመጣ ነው። ያው በቃ ተሸንፈናል።

ስለጅማ ቆይታው

ጥሩ ነው ፤ ጅማ አሪፍ ነው። ጥሩ ቆይታ ነው በውጤት ደስተኛ ባንሆንም መልካም ነገር ባይገጥመንም በሌላው ነገር ግን ጅማ ጥሩ ነበር።

ጫና ውስጥ ስለመሆናቸው

አዎ ያው ሁልጊዜ ሽንፈት ባለ ቁጥር ጫናው እየጨመረ ነው የሚሄደው እና ልጆቹም ያን ጫና የመቋቋማቸው ነገር ነው ከባድ የሆነው። ጫናው እንዳለ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ