ሪፖርት | ፋሲል የጅማ ቆይታውን በመቶ ፐርሰንት ድል አጠናቋል

በጅማ ዩንቨርሲቲ ስታድየም በተደረገው የመጨረሻ ጨዋታ ፋሲል ከነማ ድሬዳዋ ከተማን 2-0 በማሸነፍ መሪነቱን አስቀጥሏል።

ፋሲል ከነማ ዛሬም ወልቂጤን በገጠመበት አሰላለፍ ወደ ሜዳ ሲገባ ከህመም ጋር እየታገሉ ወደ ሜዳ የመጡት አሰልጣኝ ፍሰሀ ጥዑመልሳን አስጨናቂ ሉቃስ እና ሄኖክ ኢሳይያስን በእንዳለ ከበደ እና ያሬድ ዘውድነህ ቦታ በመጠቀም ጨዋታውን ጀምረዋል።

በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ፋሲል ከነማ ግቦችን ለማግኘት በሙሉ ኃይሉ በማጥቃት ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ በጥንቃቄ በመከላከል ጨዋታቸውን አከናውነዋል። ሆኖም በፋሲል ተጫዋቾች በኩል ይታይ የነበረው ከፍተኛ ጉጉት ታክሎበት ድሬዳዋ ለረጅም ደቂቃዎች የተጋጣሚውን ከፍተኛ የማጥቃት ኃይል መገደብ ችሎ ቆይቷል። ከዚህ ባለፈም የተሻሉ የግብ ሙከራዎችን ሲያደርጉ የታዩት ድሬዳዋዎች ነበሩ።

ድሬዎች ባገኙት ቀዳሚው ዕድል 14ኛው ደቂቃ ላይ ሙኸዲን ሙሳ በግራ በኩል ሳጥን ውስጥ ገብቶ ለጁኒያስ ናንጄቤ ያሳለፈውን ኳስ ናሚቢያዊው አጥቂ በቀላሉ ጎል ሊያደርገው ቢቃረብም ሚካኤል ሳማኬ አቋርጦበታል። ቀጥሎም 23ኛው ደቂቃ ላይ የሱራፌል ጌታቸውን የማዕዘን ምት ፍሬዘር ካሳ በአስደናቂ ሁኔታ በግንባሩ ቢገጭም በግቡ አግዳሚ ሊመለስበት ችሏል። የፋሲሎች የመጀመሪያው የማጥቃት ሂደት እየተቀዛቀዘ ድሬዳዋዎች ከቆሙ ኳሶች ጫና ለመፍጠር በሞከሩባቸው ቀጣይ ደቂቃዎችም 40ኛው ደቂቃ ላይ ተከላካዮች በአግባቡ ካላራቁት ኳስ ናንጄቦ ያገኘውን ዕድል በደካማ ሙከራ አባክኖችሏል።

ሆኖም ዐፄዎቹ አጋማሹ ሳይገባደድ የተጋጣሚያቸው የኋላ ክፍል ላይ የታየውን መዘናጋት ተጠቅመው 45ኛው ደቂቃ ላይ ሙጂብ ቃሲም ከሳጥን ውጪ በመታው ከባድ ኳስ የመጀመሪያውን ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርገው ፍሬው ጌታሁን አድኖባቸዋል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ግን አምሳሉ ጥላሁን ከግራ መስመር ያሻማውን እና ሙጂብ በግንባሩ የጨረፈውን ኳስ በዛብህ መለዮ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑ እጅግ የፈለገውን ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ድሬዎች የማጥቃት ተነሳሽነትን ይዘው እንደገቡ በሚጠቁም መልኩ 48ኛው ደቂቃ ላይ አስቻለው ግርማ ከሳጥን ውስጥ በመታው እና ሳማኬ በቀላሉ በያዘው ኳስ ወደ ግብ ቀርበው ነበር። ነገር ግን 56ኛው ደቂቃ ላይ ይሁን እንዳሻው ከመሀል ሜዳ ያሻገረውን ረጅም ኳስ በረከት ደስታ በግንባሩ መትቶ በአግዳሚው ሲመለስበት በድጋሚ አግኝቶ የፋሲልን መሪነት አስፍቷል። ፋሲል ጨዋታውን በመቆጣጠር ላይ ባተኮረባቸው የተቀሩት ደቂቃዎች ለወጣቶቹ ኪሩቤል ኃይሉ ፣ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ እና ለዓለምብርሀን ይግዛው የጨዋታ ሰዓትን መስጠትን መርጧል።

በሁለት ግቦች መመራት መጀመሩን ተከትሎ ድሬዳዋ አጥቅቶ ወደመጫወቱ አድልቷል። ወደ ቀኝ መስመር ያደላው የቡድኑ ጥቃት ግን ፋሲልን ጫና ውስጥ የሚከት አልነበረም። በዚህ ሂደት 74ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ሪችሞንድ ኦዶንጎ ከሙኽዲን የተፈጠረለትን ግልፅ የማግባት ዕድል መጠቀም ሳይችል ቀርቷል። ሌላ የውጤት ለውጥ ሳይታይም በፀሀያማ የአየር ፀባይ የጀመረው ውድድር በጨዋታው መገባደጃ ላይ በጣለው ካፊያ ሲጠናቀቅ ፋሲል ከነማ 2-0 ማሸነፍ ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ