በዛብህ መለዮ ጎል ካስቆጠረ በኋላ ማስተላለፍ ስለፈለገው መልዕክት ይናገራል

ፋሲል ከነማ ድሬዳዋን በረታበት ጨዋታ ቀዳሚውን ጎል በማስቆጠር የተለየ የደስታ አገላለጽ ያሳየው በዛብህ መለዮ ሀሳቡን ለሶከር ኢትዮጵያ ይናገራል።

በወሳኝ ጨዋታዎች ጎል ማስቆጠር የሚቀናው እና በተለያዩ አማራጮች መጫወት የሚችለው በዛብህ መለዮ ወደ ዐፄዎቹ ከመጣ በኃላ የተሳካ ቆይታ እያደረገ ይገኛል። ምንም እንኳን ዘንድሮ በመጀመርያዎቹ ሳምንታት ህመም አጋጥሞት የተፈለገውን አገልግሎት ባይሰጥም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ የመጀመርያ ተመራጭ በመሆን ቡድኑን እየጠቀመ ይገኛል። በዛሬው ዕለትም ሊጉን በአምስት ነጥብ ልዩነት እንዲመሩ ያስቻለችውን ቀዳሚ ጎል በማስቆጠር አንድ እጁን ወደ ጆሮው፤ ሌላኛውን ወደ አፉ በማድረግ ደስታውን የገለፀበት መንገድ አነጋጋሪ ሆኗል። እኛም ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የደስታ አገላለፁን እና ሌሎች ጥያቄዎችን አንስተንለት ተከታዩን ምላሽ ሰጥቶናል።

” ደስታዬን መግለፅ የፈለኩበትን ምክንያት ብዙም ማብራራት ባልፈልግም ሁለት ምክንያቶች ግን አለኝ። አንደኛው ከቡድናችን ጋር ተያይዞ ለሚወሩ ነገሮች ምላሽ ለመስጠት ነው። ይህን ደግሞ እነማን እንደሆኑ የደስታ አገላለፄን ሲያዩ ይገባቸዋል። ሁለተኛው ለቤተሰቦቼ ነው። ሁሌም ከጎኔ ሆነው ለሚያበረታቱኝ መልዕክት ለማስተላለፍ ነው።

” ጥሩ የውድድር ጊዜ እያሳለፍኩ ነው። ከቡና ጨዋታ በኃላ የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶብኝ የማስበውን አገልግሎት እንዳልሰጥ ዕክል ሆኖብኝ ነበር። አሁን ጠንክሬ ሠርቼ ቡድኔን ለመጥቀም እየሞከርኩ ነው። ወደ ጥሩ አቋም ለምጣት በቀን ሁለቴ ልምምድ ስሰራ ቆይቻለው። አሁን ወደ ትክክለኛ አቋሜ እየመጣው ነው። ከዚህ በኋላም ፋሲል ከነማ ወደ ዋንጫ ለሚያደርገው ጉዞ ከቡድን አጋሮቼ ጋር በመሆን አንድ ታሪክ መስራት እንፈልጋለን።

” የሠራ ያገኛል ! እስካሁን የመጣንበት መንገድም ጥሩ ነው። ዋንጫ የማናነሳበት ምክንያት የለም። ሁላችንም ለዚህ እየሠራን ነው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ