ሰበታ ከተማ ጋናዊ አጥቂ ለማስፈረም ተስማምቷል

በአሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ የሚመሩት ሰበታ ከተማዎች በዘንድሮ የውድድር ዓመት የመጀመሪያ የውጪ ዜጋ ተጫዋቾቻቸውን ወደ ስብስባቸው ለመቀላቀል ተስማምተዋል።

በዘንድሮ የውድድር ዓመት አንድም የውጪ ዜጋ ተጫዋች ሳያስፈርሙ ሊጉን የጀመሩት ሰበታ ከተማዎች የአጥቂ ክፍላቸውን ለማጠናከር ወደ ዝውውር ገበያው ገብተዋል። በዚህም የቀድሞ የመቐለ 70 እንድርታ እና ፋሲል ከነማ ተጫዋች የነበረው ኦሲ ማውሊን ወደ ስብስባቸው ለመቀላቀል የቅድመ ስምምነት ፈፅመዋል።

ይህ ጋናዊ የአጥቂ መስመር ተጫዋች 2011 ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ከመቐለ 70 እንድርታ ጋር ድንቅ ጊዜን በማሳለፍ የሊጉን ዋንጫ ማንሳቱ ይታወሳል። በተሰረዘው የውድድር ዘመንም ወደ ፋሲል ከነማ በመጓዝ ግልጋሎት ሲሰጥ ቆይቷል። በዛሬው ዕለት ደግሞ ተጫዋቹ ሶስተኛ የኢትዮጵያ ክለቡን ለመቀላቀል ቅድመ ስምምነት መፈፀሙን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘው መረጃ ያመላክታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ