የአሠልጣኞች አስተያየት | ሰበታ ከተማ 1-0 ወልቂጤ ከተማ

በሰበታ ከተማ አሸናፊነት ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ የቡድኖቹ አሠልጣኞች አስተያየታቸውን ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

አብርሃም መብራቱ – ሰበታ ከተማ

ስለ ጨዋታው?

የጨዋታው እንቅስቃሴጥሩ ነበር ማለት እቸላለሁ። ግን የዝግጅታችንን ያህል በቂ እንቅስቃሴ አይቻለሁ ማለት አልችልም። ነገርግን ሦስት ነጥብ ማግኘታችን ለተጫዋቾቻችን ስነ-ልቦና የሚጨምረው ነገር ስላለ ውጤቱ ለእኛ ጥሩ ነበር ማለት እችላለሁ።

በሁለተኛው አጋማሽ በጨዋታው ስለነበረ ለውጥ?

በእኛ በኩል ብዙ ለውጥ አላደረግንም። እንደታየው በመጀመሪያው አጋማሽ ተጫዋቾቻችን አፈግፍገው ነበር ሲጫወቱ የነበረው። በእረፍት ሰዓትም የመሐል ተከላካዮቻችንን ወደ መሐል ሜዳው አስጠግተን መጫወት እንዳለብን ተማምነናል። ይህንንም በመተግበር በጨዋታው የበላይ ሆነን ወጥተናል።

በጨዋታው ሰለነበሩ ጉዳቶች?

ከዚህ በፊት እንዳልኩት በቂ የፕሪሲዝን ጊዜ ያላሳለፉ ቡድኖች በውድድር መሐል እንደዚህ አይነት ችግሮች ያጋጥማቸዋል። ሌላኛው ደግሞ በጨዋታ መሐል የሚያጋጥሙ ግጭቶች ናቸው። እኔ እንደውም ይሄ ነገር ይቀጥላል ብዬ ነው የማስበው።

ስለቡድኑ የጨዋታ መንገድ እና ስለ ሜዳው ምቹነት?

ምንም ጥያቄ የለውም። ለምንከተለው ኳስን መሰረት ያደረገ አጨዋወት ሜዳው ምቹ ነው። እስካሁን ከተጫወትንባቸው ስታዲየሞች የባህር ዳር ስታዲየም በጣም ምቹ ነው።

ቡድኑ ሊገኝበት ስላሰበው የደረጃ ሠንጠረዥ?

አሁን የያዝነውን ጠንካራ የስነ-ልቦና ዝግጅት ለማሳደግ የመጨረሻውን የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ለመጠቀም እንሞክራለን። ጨዋታውንም በድል ደምድመን ለሁለተኛው ዙር ለመዘጋጀት እንጥራለን።

ደግአረገ ይግዛው – ወልቂጤ ከተማ

ስለ ጨዋታው?

በሁለቱም ቡድኖች በኩል የነበረው ጨዋታ ጥሩ ነበር። በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታውን ጨርሰን የምንወጣበት አጋጣሚ ነበረን። ነገርግን አለመጠቀማችን መጨረሻ ላይ ዋጋ አስከፍሎናል። መጀመሪያ በጨዋታው ልንተገብረው የነበረውን ነገር ተጫዋቾቻችን ለመተግበር የሄዱበት ርቀት የሚያስደስት ነው። ነገርግን በእንቅስቃሴዎች ውስጥ የሚገኙ አጋጣሚዎችን ያለመጠቀም ችግር ነበረብን። በተለይ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ብዙ ኳሶች ይባክኑብን ነበር። እዚህኛው የሜዳ ክልል እስክንደርስ ያለው ሂደት ጥሩ ሆኖ ሳለ መጨረሻ ላይ ግን ጥሩ አልነበረም። የእነዚህ ድምር ውጤትም ተሸንፈን እንድንወጣ አድርጎናል።

በጨዋታው ስለነበሩ ጉዳቶች?

ሲጀመር ዛሬ የተጎዱት ተጫዋቾች ከነጉዳታቸው የመጡ ተጫዋቾች ናቸው። ከጉዳት እና ኮቪድ ጋር በተገናኘ መጠቀም የነበሩብንን ተጫዋቾች አልተጠቀምንም። ሜዳውም ደረጃውን የጠበቀ ሰፊ ሜዳ በመሆኑ ጉልበት ይፈልግ ነበር። በተጨማሪም የጨዋታው እንቅስቃሴ ትንሽ ግጭቶችም የበዙበት ነበር። ሳንፈልግ በለወጣናቸው ተጫዋቾች ምክንያት አጨዋወታችን ላይ ተፅዕኖ አድርጓል። ግን ተጫዋቾቼ ያለውን ነገር ተቋቁመው ውጤት ይዞ ለመውጣት ያደረጉት ነገር እጅግ የሚያስደስት ነው። ዛሬ የታዩብንን ክፍተቶች በማረም ለቀጣይ ጥሩ ለመጫወት እንሞክራለን።

ከጨዋታው ዳኝነት ጋር በተያያዘ?

እኔም በጨዋታ ስሜት ውጥ ሆኜ ዳኝነቱን ስለምቆጣጠረው ይህ ነው ብሎ መናገር ይከብዳል። በእርግጥ ግን ጉልህ የነበሩ ስህተቶች ነበሩ። በተለይ የመስመር ዳኞቹ ላይ አንዳንድ ክፍተቶችን ስናይ ነበር። ስህተቶች ይኖራሉ። ግን በዚህ ደረጃ ዋጋ የሚያስከፍሉ ስህተቶች ትንሽ አስቸጋሪ ናቸው። ሆኖም ግን በትክክል ዳኞችን የሚገመግም አካል አለ ብዬ አስባለሁ። በተረፈ ግን ተጫዋቾቻችን ጫና ውስጥ እንዲገቡ እና ከጨዋታ መንፈስ እንዲወጡ አድርጓል። በአጠቃላይ ግን ከዛሬው ጨዋታ ብዙ ትምህርቶችን ይዘን ወተናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ