​ቅድመ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ አዳማ ከተማ

በጊዮርጊስ እና አዳማ ጨዋታ ላይ የሚያጠነጥኑ ሀሳቦችን የተመለከትንበትን ዳሰሳችንን እነሆ ብለናል።

እስካሁን ባለው ሁኔታ የዋንጫ ፉክክር ውስጥ ካሉት አራቱ ቡድኖች ውስጥ ዝቅ ብሎ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፉክክሩ እንዳይነጠል የነገዎቹ ሦስት ነጥቦች ያስፈልጉታል።

ከአሰልጣኝ ማሂር ዴቪድስ ጋር የቀጠለው ጊዮርጊስ ከአስቻለው ታመነ ውጪም ለተጋጣሚዎቹ በቀላሉ የማይደፈር ሆኖ ቀጥሏል። የቡድኑ አንገብጋቢ ችግር ግን ግብ የማስቆጠር ብቃቱ መውረድ ሆኗል። በሰባት ጨዋታዎች 17 ግቦችን ከመረብ አሳርፎ የነበረው ጊዮርጊስ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ከአንድ ጊዜ በላይ ኳስ እና መረብን ማገናኘት አልቻለም። ያሉትን አጥቂዎች በቁጥር አበርክቶ ወደ ሜዳ መግባት አዋጭ እየሆነለት የሚገኝ የማይመስለው ቡድኑ የቀደመውን የግብ ማግኛ ቀመሩን ፈልጎ ማግኘት የግድ ይለዋል። እርግጥ ነው የነገ ተፋላሚው በርካታ ግቦችን በማስተናገድ በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው አዳማ መሆኑ ቡድኑ ከግብ ጋር እንዲታረቅ ሊረዳው ይችላል። ነገር ግን እንደ ሲዳማ እና ወላይታ ድቻ ዓይነት ተጋጣሚዎቹ ላይ ሲቸገር የታየው የፈረሰኞቹ የማጥቃት ዕቅድ እክል ላያጣው ይችላል። እርግጠኛ መሆን የሚቻለው ግን ቡድኑ ከጅማ የመጨረሻ ጨዋታዎቹም በላይ ከፍ ባለ ጀብደኝነት ለማጥቃት እንደሚገባ ነው።

የጅማ ቆይታውን በሽንፈት ደምድሞ የነበረው አዳማ ከሰነበተበት ወራጅ ቀጠና ቀና ለማለት ነገ ሌላ ፈተናን ይጋፈጣል።

አዳማ ከተማ እጅግ ወርዶ ይታይ ከነበረባቸው የቀደሙት ጨዋታዎች እየተሻሻለ መታየቱን መናገር ይቻላል። ሆኖም መልካም አቋም ላይ የመገኘት ብቃትን ማስቀጠል ላይ እንደብዙዎቹ ቡድኖች እየተፈታነ ይገኛል። ይህ በመሆኑም ነው እምብዛም መጥፎ ባልነበረበት የሰበታው ጨዋታ አስደናቂ  ቀን ያሳለፈበትን የሀዋሳውን ብቃቱን መድገም ባለመቻሉ ለሽንፈት ተዳርጎ የነበረው። ቡድኑ ነገም ዝቅተኛ ግምት ቢሰጠው እንኳን የሀዋሳውን ገድሉን አይደግምም ማለት አይቻልም። በተለይም የዛን ቀኑን የመልሶ ማጥቃት ስልነቱን መልሶ ማግኘት ከቻለ ተጋጣሚው አልፎ አልፎ በዚህ ረገድ የሚታይበትን ድክመት የመጠቀም ዕድል ይኖረዋል። በመከላከሉም ረገድ ቢሆን በድጋሚ ሀዋሳ ላይ የተገበረውን የመስመር ጥቃትን የመከላከል ዘዴ ሳያዛንፍ ጥቅም ላይ ማዋል ይኖርበታል። እንደጨዋታው ክብደትም እንደ አብዲሳ ጀማል ዓይነት ተጨዋቾች የግል ብቃት ጥሩ ደረጃ ላይ መገኘት ነገ ለአዳማ በእጅጉ ያስፈልገዋል።

የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተከላካይ አስቻለው ታመነ የቀጥታ ቀይ ካርዱን የመጨረሻ የቅጣት ቀን ነገ የሚያሳልፍ ይሆናል። አዳማ ከተማ ደግሞ አምበሎቹ ሱሌይማን መሀመድ እና የኋላሸት ፍቃዱን በጉዳት ሲያጣ ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ ደግሞ እንዳገገመለት ሰምተናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ጊዮርጊስ እና አዳማ እስካሁን በሊጉ 36 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 18 በማሸነፍ የበላይ ሲሆን አዳማ 7 ጨዋታ አሸንፏል። 11 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

– በግንኙነቶቹ ጊዮርጊስ 45 ፤ አዳማ ከተማ 24 አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)

ለዓለም ብርሀኑ

ደስታ ደሙ – አማኑኤል ተረፋ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ሄኖክ አዱኛ

ሀይደር ሸረፋ – ናትናኤል ዘለቀ

ጋዲሳ መብራቴ – ሮቢን ንግላንዴ – አቤል ያለው

ጌታነህ ከበደ

አዳማ ከተማ (4-3-3)

ታሪክ ጌትነት

ታፈሰ ሰርካ – ደስታ ጊቻሞ – ትዕግስቱ አበራ – አካሉ አበራ

ቴዎድሮስ ገ/እግዚያብሄር – ደሳለኝ ደባሽ  – በቃሉ ገነነ

በላይ አባይነህ – አብዲሳ ጀማል – ፍሰሀ ቶማስ