ዋልያዎቹ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ለማግኘት ተቃርበዋል

ካሜሩን ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታቸውን እያደረጉ የሚገኙት ዋልያዎቹ ከሁለት ሀገራት ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ ለማድረግ ንግግር ላይ መሆናቸው ታውቋል።

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከኮትዲቯር፣ ማዳጋስካር እና ኒጀር ጋር ተደልድሎ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታውን እያደረገ ይገኛል። ካከናወናቸው አራት ጨዋታዎች ስድስት ነጥቦችን በመያዝ የምድቡ አምስተኛ እና ስድስተኛ ጨዋታዎቹን በመጠባበቅ ላይ የሚገኘው ቡድኑ ከጨዋታዎቹ በፊት ጠንካራ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ለማድረግ እየጣረ ይገኛል። ሶከር ኢትዮጵያ እንዳገኘው መረጃ ከሆነ ደግሞ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከመጋቢት አጋማሽ ጀምሮ ከሚደረጉት ወሳኝ ጨዋታዎች በፊት ከማላዊ እና ታንዛኒያ ብሔራዊ ቡድኖች ጋር ቡድኑ እንዲጫወት እየጣረ ይገኛል።

በምድብ 11 የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በነጥብ (7) እኩል ሆነው በእርስ በእርስ ግንኙነት በተበላለጡት ኮትዲቯር እና ማዳጋስካር ተበልጦ የምድቡ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።


© ሶከር ኢትዮጵያ