ጅማ አባጅፋር ሁለት ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል

አሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያምን በመሾም ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት እየጣሩ የሚገኙት ጅማ አባጅፋሮች ተጨማሪ ሁለት ተጫዋቾችን ማስፈረማቸው ታውቋል።

ቡድኑን የተቀላቀለው የመጀመሪያው ተጫዋች ሥዩም ተስፋዬ ነው። የቀድሞው የመብራት ኃይል፣ ደደቢት እና ከ2010 ጀምሮ ደግሞ ለመቐለ 70 እንደርታ እየተጫወተ ቆይቶ በመጀመሪያው ዙር የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ወደ ሠራተኞቹ አቅንቶ ግልጋሎት የሰጠው ሥዩም ከሳምንታት በፊት ከወልቂጤዎች ጋር በስምምነት ከተለያየ በኋላ በዛሬው ዕለት አዲስ ቡድን አግኝቷል። ለረጅም ዓመታት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተጫወተው ተጫዋች ጅማን መቀላቀልም በደረጃ ሠንጠረዡ ግርጌ ላይ ላለው ክለብ ጥሩ ዜና ነው።

ሁለተኛው ተጫዋች ደግሞ የግብ ዘቡ በረከት አማረ ነው። በወልዋሎ፣ አውሥኮድ እና ኢትዮጵያ ቡና የተጫወተው በረከት በክረምቱ ወደ መቐለ አምርቶ የነበረ ቢሆንም ክለቡ በሊጉ እየሳተፈ አለመሆኑን ተከትሎ በዚህ ዓመት ሳይጫወት ቆይቶ በዘንድሮው ውድድር ሁለተኛ ብዙ ግብ ያስተናገደውን ክለብ ለማጠናከር እንዲሁም ከአቡበከር ኑሪ እና ጃኮ ፔንዜ ጋር ተፎካክሮ የክለቡ ቋሚ የግብ ዘብ ለመሆን ጅማ ደርሷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ