ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | አዲስ አበባ ከተማ አርባምንጭን አሸንፏል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የአስራ አራተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ በአዲስ አበባ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ከተማ መካከል ተደርጎ አዲስ አበባ ከተማ 2ለ0 አሸናፊ ሆኗል፡፡

ብዙም በእንቅስቃሴ ማራኪ ባልታየበት ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማዎች በረጃጅም እና ተሻጋሪ ኳሶች እድል ፈጥረዋል፡፡ 10ኛው ደቂቃ ላይም ከቀኝ አቅጣጫ በረጅሙ በሻዱ ስታሻማ የአርባምንጯ ግብ ጠባቂ ነህሚያ አብዲ ኳሱን በአግባቡ መቆጣጠር ባለመቻሏ ቤተልሄም ሰማን በፍጥነት አግኝታው ከመረብ አገናኝታ አዲስ አበባ ከተማን መሪ አድርጋለች፡፡

የአርባምንጮች የመከላከል ድክመት ሳይሻሻል በቀጠለበት ቀሪ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በተወሰነ መልኩ በረጅሙ ወደ መሠረት ወርቅነህ በማሻገር ወደ አዲስ አበባ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም ላገኟቸው ኳሶች የመጨረሻ ውሳኔዎቻቸው ደካማ በመሆኑ አቻ ለመሆን አልታደሉም፡፡ በአንፃሩ ረጃጅም ኳሶቻቸው አዋጭ መስሎ የታያቸው አዲስ አበባ ከተማዎች በድጋሚ በቤተልሄም ሰማን አማካኝነት ጎል ቢያስቆጥሩም ከጨዋታ ውጪ ተብሎባቸዋል፡፡ 44ኛው ደቂቃ ላይ ከመሀል ሜዳ መሬት ለመሬት የተሰጣትን ኳስ ሰላማዊት ሀይሌ ብቻዋን አንድ ለአንድ ከግብ ጠባቂዋ ነህሚያ ጋር ተገናኝታ ብትመታውም ግብ ጠባቂዋ በግሩም ሁኔታ መልሳባታለች፡፡

ከእረፍት መልስ በተወሰነ ረገድ አርባምንጭ ከተማዎች ተሻሽለው መቅረብ የቻሉ ቢሆንም አሁንም በአጥቂ ክፍላቸው ይታይ የነበረው ክፍተት ግን በዚህኛውም አጋማሽ ሳይስተካከል ቀጥሏል፡፡ብዙም ሙከራዎችን ባላስመለከተን ጨዋታ ኤደን ላይላ ቅፅበታዊ በሆነ ፈጣን የመስመር አጨዋወት የተገኘን ኳስ ከግቡ ትይዩ አግኝታ የሳተቻት አስቆጪ ሙከራ አቻ የምታደርጋቸው የነበረች ቢሆንም ወደ ጎልነት መለወጥ ሳትችል ቀርታለች፡፡ ከዚህች ሙከራ ባሻገር መሠረት ወርቅነህ ሌላ አጋጣሚን ብታገኝም ሳትገቀምበት ቀርታለች፡፡

55ኛው ደቂቃ ላይ ሰላማዊት ኃይሌ ከቀኝ በኩል ለማሻማት የላከቻት ኳስ ከመረብ አርፋ በቀሩት ደቂቃዎች ተጨማሪ አንድም አጋጣሚዎችን መመልከት ሳንችል ጨዋታው በአዲስ አበባ ከተማ 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የአዲስ አበባ ከተማዋ ሰለማዊት ኃይሌ የጨዋታው ምርጥ ተብላ ተሸልማለች፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ