“ነገ ግዴታ ማሸነፍ አለብን” – ታፈሰ ሰለሞን

ነገ ረፋድ ላይ በፋሲል ከነማ እና በኢትዮጵያ ቡና መካከል ከሚካሄደው እጅጉን ወሳኝ ጨዋታ አስቀድሞ ታፈሰ ሰለሞን የሚናገረው አለው።

የነገዎቹ ተጋጣሚዎች የአምስት ነጥቦች ልዩነት ተበላልጠው የደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ይገኛሉ። ዐፄዎቹ ከኢትዮጵያ ቡና ያላቸውን የነጥብ ልዩነት በማስፋት ወደ ዋንጫ የሚያደርጉትን ጉዞ ያሳምራሉ ወይስ ቡናማዎቹ ጨዋታውን በማሸነፍ ከመሪው ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት በማጥበብ የዋንጫ ተፎካካሪነታቸውን በሚገባ ያሳያሉ የሚለውን ነገ ረፋድ ላይ የምናይ ይሆናል። ታዲያ ከነገው እጅግ ወሳኝ ጨዋታ አስቀድሞ የኢትዮጵያ ቡናው የመሐል ሜዳ ሞተር ታፈሰ ሰለሞን ለሶከር ኢትዮጵያ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥቷል።

” ለነገው ጨዋታ ብለን የተለየ ዝግጅት አላደረግንም። ሆኖም ጨዋታው ለእኛ በጣም ወሳኝ ነው። ምክንያቱም መሪው እንዳይርቀን እየተከተልን ነው። የነገው ጨዋታ የተለየ ግምት ባንሰጠውም ለማሸነፍ ነው የምንጫወተው

” በወልቂጤ ጨዋታ ወቅት ትንሽ ብልጫ ተወስዶብን ነበር። ይህንን ስህተታችን ቀርፈን ለመምጣት ስንሰራ ቆይተናል። በነገው ጨዋታም ኳሱን በሚገባ ተቆጣጥረን ተጭነናቸው ለመጫወት አስበናል። ለማሸነፍ ነው የምንመጣው፤ እናሸንፋለን የሚል ግምት አለን። ፋሲል ቀላል ቡድን እንዳልሆነ እናውቃለን። ስለዚህ ትንሽ ከበድ ሊለን ይችላል። መሐል ላይ ብዙ ብልጫ ላይወስዱብን ይችላሉ። በተለይ በመስመር በኩል በሽመክት ጉግሳ እና በረከት ደስታ በኩል እንቅስቃሴያቸው ሊያስቸግረን ይችላል።

” ከነገው ጨዋታ የምነፈልገው ማሸነፍ ብቻ ነው። ምክንያቱም ከዚህ ጨዋታ ሽንፈት የሚያጋጥመን ከሆነ በስምንት ነጥብ የሚርቀን ስለሆነ ነገ ግዴታ ማሸነፍ አለብን። የግዴታ ማሸነፍ እንዳለብን ነው የምናስበው። ዘንድሮ ደግሞ ቡድናችን ከመቼውም ጊዜ የተሻለ ቡድን አለን። ለዚህም ውጤቱ ማሳያ ነው። የተሻለ ደረጃ ለመድረስ ደግሞ ነገ ማሸነፍ አለብን፤ የሚያስፈራን ነገር የለም።

” የቡድን መንፈሳችን በሚገርም ሁኔታ ላይ ይገኛል። ሁላችንም ተከባብረን ተፋቅረን እየሰራን ነው። አንድነታችን በጣም ደስ የሚል ነው። ያም ነው ለዚህ ውጤት ያበቃን እንጂ የተለየ ስብስብ ኖሮን አይደለም። በወጣት የተገነባ ቡድን ነው አሰልጣኝ ካሣዬ የሰራው። የአሰልጣኛችን ብቃት እንዳለ ሆኖ የቡድን መንፈሳችን በጣም አሪፍ ነው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ