የአሠልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 0-0 ድሬዳዋ ከተማ

ያለግብ አቻ ከተጠናቀቀው የከሰዓት ጨዋታ በኋላ ሱፐር ስፖርት ከቡድኖቹ አሠልጣኞች አስተያየት ተቀብሏል።

ማሒር ዴቪድስ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለ ጨዋታው?

በመጀመሪያው አጋማሽ ፍጥነት የለንም ነበር። ኳሱን በደንብ ብናንሸራሽርም የማጥቂያ ቦታዎችን ለማግኘት ፍጥነት አልነበረንም። በመስመሮች ላይ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ስንሞክር ነበር። ግን ጥቃቶቻችን ፍጥነቶቻቸው የወረደ ነበር። በአጠቃላይ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ስንደርስ ጥሩ ነበር። ግን እድሎችን ስናገኝ መጠቀም አልቻልንም።

ስለ ዋንጫ ፉክክሩ እና የነገ ጨዋታ?

ዛሬ ሁለት ነጥብ ጥለናል። አሁንም ግን ወደፊት መገስገሳችንን አናቆምም። የነገውን የኢትዮጵያ ቡናን እና ፋሲል ከነማን ጨዋታንም እንከታተላለን። አሁን ግን በቀጣይ የሚገጥመን ሀዋሳ ላይ ነው ትኩረታችን። ከዛ ጨዋታ ሦስት ነጥብ ማግኘትን ነው የምናስበው።

ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ – ድሬዳዋ ከተማ

ስለ ጨዋታው?

ባለፉት ከነበሩት ሁለት ጨዋታዎች የተሻልን የነበርንበት ጨዋታ ነበር። በሊጉ ላይ መቆየት ከፈለግን እንደዛሬው አይነት እና ብልጫ የወሰድንባቸውን ጨዋታዎችንም ማሸነፍ አለብን። በአጠቃላይ ሜዳ ላይ ከነበረን ብልጫ ሦስት ነጥብ ይዘን መውጣት ነበረብን። ግን አጨራረስ ላይ ክፍተቶች ነበሩብን። ይህኛው ክፍተታችን ላይም እንሰራለን።

ቡድኑ ጥሩ ጥሩ ግልፅ የግብ ማግባት ዕድሎችን ፋጥሮ ጎል ስላለማስቆጠሩ?

ይህንን ችግር እንደ ቡድን ነው የምንወስደው። እንዳልኩት ከባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ቡድናችን ተሻሽሎ ነው የመጣው። ተጫዋቾቻችን ያላቸው አቅም እና ቡድኑ ያለበት ደረጃ የሚመጣጠን እንዳልሆነ ነው ዛሬ ያየሁት። በደንብ ጫና አሳድረን ተጫውተናል። ግን ብልጫ ወስደን ተጫውተን ሦስት ነጥብ አለማግኘታችን በቀጣይ ስራ እንደሚጠብቀን የሚያሳይ ነው። እንደተባለው ብዙ ዕድሎችን ብንፈጥርም መጠቀም አልቻልንም። በቀጣዩ የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ችግራችንን አስተካክለን እንቀርባለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ