“ነገ ደጋፊዎቻችን ከእኛ ጥሩ ነገር ይጠብቁ” ሀብታሙ ተከስተ

ነገ ረፋድ ከሚደረገው ተጠባቂው የኢትዮጵያ ቡና እና ፋሲል ከነማ ጨዋታ በፊት የዐፄዎቹ የአማካይ መስመር ተጫዋች ስለ ጨዋታው አጭር ቆይታን ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አድርጓል።

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ዙር ውድድሩን በባህር ዳር ከተማ እያከናወነ ይገኛል። በባህር ዳር ከሚደረጉ ወሳኝ ጨዋታዎች መካከል አንዱ ደግሞ ነገ ረፋድ አራት ሰዓት የሚደረገው የኢትዮጵያ ቡና እና ፋሲል ከነማ ጨዋታ ነው። ለዋንጫ የሚፎካከሩት ሁለቱ ቡድኖች ከሚያደርጉት ጨዋታ አስቀድሞም የሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ የአማካይ መስመር ተጫዋች የሆነው ሀብታሙ ተከስተ ስለ ጨዋታው ተከታዩን ሀሳብ አጋርቶናል።

“ከቀናት በፊት ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፈናል። ነገ ደግሞ ኢትዮጵያ ቡናን እንገጥማለን። ቡና ዘንድሮ ጥሩ እና ከባድ ቡድን ነው። ይህ ቢሆንም ግን እስካሁን ለሌሎቹ ቡድኖች የምናደርገውን ዝግጅት ነው ለነገውም ጨዋታ እያደረግን ያለነው።

“የነገው ጨዋታ ጥሩ ፉክክር የሚታይበት ይመስለኛል። ቡናዎች ኳስ ይዘው መጫወት የሚፈልጉ ናቸው። እኛም በተመሳሳይ ከኳስ ጋር መጫወት እናዘወትራለን። ብቻ ማራኪ ጨዋታ እንደሚሆን እገምታለሁ።

“አቡበከር ጎበዝ እና ጨራሽ አጥቂ ነው። እኔም በጣም ነው የማደንቀው። ልዩ ክብርም አለኝ። ነገ በሚኖረን የሜዳ ላይ የአንድ ለአንድ ፍልሚያ ግን እኔ ሥራዬን ተወጥቼ እንደማሸንፈው ነው የማስበው።

“ነገ ብናሸንፍም ዋንጫውን እንዳገኘን አንቆጥርም። ገና ቀሪ ጨዋታዎች አሉ። ሌሎች በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ያሉ ቡድኖችን ገና እንገጥማለን። ስለዚህ ጊዜው ገና ነው። በመጨረሻም ግን ነገ ደጋፊዎቻችን ከእኛ ጥሩ ነገር ይጠብቁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ