​ሪፖርት | ባህር ዳር ከተማ የመጀመሪያውን ተከታታይ ድል አስመዝግቧል

በ15ኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ ሀዲያ ሆሳዕናን 1-0 ማሸነፍ ችሏል።

ባህር ዳር ከተማ ከሲዳማው ድል አፈወርቅ ኃይሉን በሳምሶን ጥላሁን ለውጦ ወደ ሜዳ ሲገባ ከወላይታ ድቻው ሽንፈቱ ሦስት ለውጦች ያደረገው ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ ሄኖክ አርፌጮ ፣ አማኑኤል ጎበና እና ዱላ ሙላቱን በአክሊሉ አያናው ፣ ተስፋዬ አለባቸው እና መድሀኔ ብርሃኔ ተክቷል።

አካላዊ ፍትጊያ እና ብርቱ ፍልሚያዎችን ያሳየን የመጀመሪያው አጋማሽ በአመዛኙ በሀዲያ ሆሳዕና ሜዳ ላይ ያመዘነ ነበር። በጨዋታው ግጭት በመበርከቱ ኳስ መስርተው መሀል ሜዳ ላይ ቅብብሎችን እንደልብ ለመከወን ብዙ ዕድሉ ያልነበራቸው ባህር ዳሮች በተጋጣሚያቸው ሳጥን ውስጥ የተገኙባቸው አጋጣሚዎች ግን ጥቂት የሚባሉ አልነበሩም። ያም ሆኖ በቁጥር በርከት ብለው የግብ ክልላቸውን ሲከላከሉ የነበሩት የአሸናፊ በቀለ ልጆች ኳሶችን ተደርቦ በማውጣት እና ቅብብሎችን በማቋረጥ ባህር ዳር በጨዋታው ጎል እንዳያገኝ አድርገዋል።

4ኛው ደቂቃ ላይ የፍፁም ዓለሙ ጥሩ ቅጣት ምት ተጨርፎ የወጣባቸው ባህር ዳሮች 22ኛው ደቂቃ ላይ ኳስ በእጅ ተነክቶ ጨዋታው በቅጣት ምት ቀጠለ እንጂ ከማዕዘን የተነሳ እና የተጨረፈውን ኳስ ወሰኑ ዓሊ ለማስቆጠር ታቃርቦ መድሀኔ ብርሀኔ ከግብ መስመር ላይ አውጥቶበት ነበር። በሌላ የጣና ሞገዶቹ ሙከራ 28ኛው ደቂቃ ላይ ግራማ ዲሳሳ በግራው የሳጥኑ ክፍል ከፍፁም ዓለሙ የተቀበለውን ኳስ በደንብ ሳይወስን ሞክሮ ወደ ውጪ ወጥቶበታል። 

ተጋጣሚያቸውን ከከባድ ሙከራ ማገድ የቻሉት ሀዲያ ሆስዕናዎች በመልሶ ማጥቃት ከሜዳቸው ለመውጣት ሲሞክሩ ፊት ላይ ካላቸው አነስተኛ የተጨዋቾች ቁጥር አንፃር  ኳሶች እየተበላሹባቸው ለባህር ዳር ጥቃት ሲጋለጡ ቢታዩም 33ኛው ደቂቃ ላይ አይደክሜው ቢስማርክ አፒያ ከሳጥን ውስጥ በጠንካራ ምት ያደረገው ሙከራ ወደ ላይ ተነሰባት እንጂ ከባድ የሚባል ነበር።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር አዲስ ህንፃ እና ዱላ ሙላቱን ቀይረው በማስገባት የአደራደር ለውጥ ያደረጉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ተነቦባቸዋል። መካከለኛ ርቀት ባላቸው ከመሀል በሚነሱ ኳሶች ወደ ፊት ለመሄድ የሚጥሩበት መንገድ ግን ኢላማቸውን የጠበቁ የግብ ሙከራዎችን ሲያስገኝላቸው አልታየም። ይልቁኑም በመከላከል ወቅት አምስት ተጨዋቾችን ከኋላ ይደረድር የነበረው ቡድን በአንድ መቀነሱ ለባህር ዳሮች የተሻለ ነፃነትን ሰጥቷል። 54ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ዓለሙ በቀኝ መስመር በኩል ከፍቅረሚካኤል ዓለሙ የተላከለትን ኳስ ይዞ በመግባት በአደገኛ ሩጫ በሳጥን ውስጥ ደርሶ ሞክሮ መሀመድ ሙንታሪ ያዳነበት ሙከራ የጨዋታው የመጀመሪያ በእጅጉ ለግብ የቀረበ የግብ ዕድል ነበር ማለት ይቻላል። 

የግራ ወገን የቡድናቸው ማጥቃት የተሻለ ዕድል ቢያገኝም በተደጋጋሚ ኳሶች መበላሻቸውን በማየት አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ሣለአምላክ ተገኘን በግርማ ዲሳሳ ምትክ ማስገባታቸው በአንድ ደቂቃ ልዩነት ለውጥ አምጥቶላቸዋል። 63ኛው ደቂቃ ላይ ሳምሶን ጥላሁን በግሩም ሁኔታ ያሳለፈለትን ኳስ ተጫዋቹ በግራ የሳጥኑ ክፍል በመግባት አክርሮ መትቶ ማስቆጠር ችሏል።

በቀሪዎቹ ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል እንደ ሚካኤል ጆርጅ እና ምንይሉ ወንድሙ ዓይነት ተጨዋቾች ወደ ሜዳ ቢገቡም በማጥቃቱ ረገድ ዓይን የሚገባ የጨዋታ ሂደት አልተመለከትንም። ተስፋዬ አለባቸው ፍፁም ዓለሙ ላይ በሰራው ጥፋት በጭማሪ ደቂቃ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ከወጣበት ክስተት በኋላም የኢንተርናሽናል አርቢትር ለሚ ንጉሴ ፊሽካ ተሰምቷል።

በውጤቱም ባህር ዳር የመጀመሪያ ተከታታይ ድል ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ የመጀመሪያ ተከታታይ ሽንፈት ሲያስመዘግቡ በደረጃ ሰንጠረዡም ቦታ ተቀያይረው ባህር ዳር ወደ አራተኝነት ከፍ ብሏል።