“የተዘጋጀሁበትን ነው እያገኘሁ ያለሁት” ረሒማ ዘርጋው

👉 “የመጀመሪያ ዕቅዴ ከክለቤ ጋር ዋንጫ ማንሳት ነው”
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ሊጠናቀቅ የሁለት የጨዋታ ሳምንት ዕድሜ ብቻ ቀርቶታል። ከተከታዩ መከላከያ በአራት ነጥቦች የራቀው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም የሊጉን ዋንጫ ከአምስት ዓመታት በኋላ ለማንሳት ቀጣዩን መርሀ ግብር ይጠብቃል፡፡ ዘንድሮ ቡድኑ በዚህ ደረጃ እንዲገኝ ጉልህ ሚና እየተወጡ ከሚገኙ ተጫዋቾች መካከል አጥቂዋ ረሂማ ዘርጋው ግንባር ቀደሟ ናት። ቡድኑን በአጥቂነት እና በአምበልነት እየመራች ለክለቧም አስራ ስድስት ግቦችን በማስቆጠር የግብ አስቆጣሪነት ደረጃውን ከሎዛ አበራ በአንድ በልጣ እየመራች የምትገኘው ተጫዋቿ እያሳለፈች ስላለው ወቅታዊ አቋሟ እና ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ ኮከብ ተጫዋች አልያም ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ስለማጠናቀቅ ስለማሰቧ ለሶከር ኢትዮጵያ ትናገራለች፡፡

“ዓመቱን ሊጉን እየመራንበት እንገኛለን። ከንግድ ባንክ ጋርም ጥሩ ጊዜ እያሳለፍን እንገኛለን፡፡ በግሌ ዘንድሮ በደንብ ተዘጋጅቼ መጥቻለሁ፤ የተዘጋጀሁበትም እያሳየሁ ነው፡፡ ያው ፉክክሩም ደግሞ የቶርናመንት ባህርይ ያለው ስለሆነ ያለህን ነገር ወዲያው ወዲያው እያሻሻልክ ራስህንም እያረምክ የምትመጣበት ውድድር ነው፡፡ እኔ በበኩሌ የተዘጋጀሁበትን ነው እያገኘሁ ያለሁት።

“የመጀመሪያ ዕቅዴ ዕውነት ለመናገር ከክለቤ ጋር ዋንጫ ማንሳት ነው፡፡ ከዛ ቀጥሎ ግን እንደ አጥቂነቴ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ለመሆን ነው ያሰብኩት። በጥሩ ሁኔታ እየሄድኩ ነው፤ ከፈጣሪ ጋር ሁሉንም እንደማሳካ ዕርግጠኛ ነኝ።

“ትልቁ የቡድናችን ጥንካሬ ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች መጥተዋል የነሎዛ፣ ሰናይት እና ሌሎች መምጣት ቡድናችንን አጠናክሮታል። ቡድኑ ውስጥም ያለን ተጫዋቾች ግዴታ ከሌሎቹ ጋር ለመፎካከር አቅማችንም ከባድ ስለሆነ ዘንድሮ ዋንጫ መብላት እንዳለብን እየተነጋገርን ነበር። እንግዲህ ከፈጣሪ ጋር ደግሞ መንገዱን ይዘነዋል፡፡ ያለን ስሜት፣ አንድነታችን፣ እርስ በእርስ መነጋገራችን ይሄን ውጤት አምጥቶልናል። ከአሰልጣኝ ብርሀኑ እና ስታፉ ጋር አንድ ላይ በመሆን ማለት ነው”፡፡

“ካለፉት ዓመታት ዘንድሮ ፉክክሩ በመጀመሪያውም በሁለተኛው ዙር በጣም ከባድ ነው፡፡ ትልልቅ ቡድኖች ነጥብ የሚጥሉበት ነው፡፡ከመከላከያ እና ሀዋሳ በትንሽ ነጥብ ነው የምንራራቀው። ጠንካራ ቡድኖች ቢሆኑም እኛ ከቀጣይ ሁለቱ ጨዋታዎች ላይ የመጀመሪያውን ካሸነፍን ዋንጫውን እናረጋግጣለን። መከላከያ እና ሀዋሳ እርስ በእርስ ስለሚገናኙ እነሱን ጥለን ለመሄድ ነው የምናስበው። በሰፊ ነጥብ ነው ዋንጫውን ማንሳት የምንፈልገው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ