ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ንግድ ባንክ ወደ ዋንጫው የተጠጋበትን ድል አስመዝግቧል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የአስራ ስድስተኛ ሳምንት አራተኛ ጨዋታ በሊጉ አናት ተከታትለው የሚገኙት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሀዋሳ ከተማን አገናኝቶ የሎዛ አበራ ብቸኛ ጎል ንግድ ባንክ 1ለ0 አሸናፊ አድርጋለች፡፡

የመሐል ሜዳ ፍትጊያ በዝቶ የታየበት እና ተመጣጣኝ ፉክክርን ያሳየን የመጀመሪያው አጋማሽ ሁለት የጨዋታ መልክ ነበረው ማለት ይቻላል፡፡ በአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው የሚመራው ንግድ ባንክ አብዛኛዎቹን የጨዋታ ደቂቃዎች በሀዋሳ የእንቅስቃሴ የበላይነት የተወሰደበት ሲሆን ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታ ሪትም በመመለስ ጨዋታው ወደ ተመጣጣኝ ቅርፅ እንዲመለስ አስችሏል፡፡ ሀዋሳ ከተማዎች ኳስን በመቀባበል ይበልጥ የማጥቂያ መንገዳቸውን ወደ ግራ አዘንብለው ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት አድርገዋል፡፡ በዚህ የጨዋታ መንገዳቸውም ፈጣኗን መሳይ ተመስገንን ማዕከል በማድረግ ጥቃት በመሰንዘሩ ቀዳሚ ሆነዋል፡፡ ዙፋን ደፈርሻ ባደረገችው ሙከራ ወደ ንግድ ባንክ የግብ ክልል የደረሱት ሀዋሳዎች 15ኛው ደቂቃ ላይ ለግብ የቀረበ ዕድልን ፈጥረዋል፡፡ መሳይ ተመስገን ከቅጣት ምት ከግራ የንግድ ባንክ በቀጥታ አክርራ መታ ግብ ጠባቂዋ ንግስቲ መዐዛ በአግባቡ መቆጣጠር ባለመቻሏ አጠገቧ የነበረችሁ ዙፋን ደፈርሻ አግኝታ አስቆጠረች ሲባል ኳሱን ስተመታ ጥንካሬ ስላልነበረው በቀላሉ ንግስቲ ይዛባታለች፡፡

የጨዋታውን እንቅስቃሴ ያጠኑ የሚመስሉት ንግድ ባንኮች ከሀያ አምስተኛው ደቂቃ በኃላ በሰናይት ቦጋለ ከሚመራው የመሀል ክፍል ወደ ግራ በኩል በተሰለፈችው አረጋሽ ካልሳ የማጥቃት ኃይላቸውን ሙሉ በሙሉ በማድረግ ጎል ለማግኘት ታትረዋል፡፡22ኛው ደቂቃ ላይ አረጋሽ ካልሳ ከቅጣት ምት ስትመታ የሀዋሳ ተከላካዮች ኳሷን በአግባቡ ማራቅ ሳይችሉ ቀርተው አየር ኳሷ እያለች በቅፅበት ረሂማ አግኝታ በግንባሯ ብትገጭም ገነት ኤርሚያስ ይዛባታለች፡፡

በንግድ ባንክ በሂደት ለመበለጥ ይገደዱ እንጂ ሀዋሳ ከተማዎች ሙከራ ከማድረግ ወደ ኃላ አላሉም 29ኛው ደቂቃ ላይ አጥቂዋ መሳይ ተመስገን ከቅጣት ምት ወደ ጎል በቀጥታ መታ የግቡ የላይኛው ቋሚ ብረት ገጭቶ የመለሰባት ሀዋሳዎች ምናልባት መሪ ልታደርግ የምትችል ከሙከራዎች ሁሉ የጠራች ዕድል መሆን ብትችልም ወደ ጎልነት ልትለወጥ ግን አልቻለችም፡፡

33ኛው ደቂቃ ላይ ንግድ ባንኮች ጎል አስቆጥረዋል፡፡ የሀዋሳ ተከላካዮች ክፍተትን የተመለከተችው አረጋሽ ካልሳ መሬት ለመሬት ወደ ግብ ክልል በቀጥታ የላከቻትን ኳስ ሎዛ አበራ በቀላሉ ወደ ግብነት ለውጣ ንግድ ባንክን ቀዳሚ አድርጋለች፡፡ ከጎሏ በኃላ በረሂማ ዘርጋው አማካኝነት ሌላ ግብ ባንኮች ቢያገኙም ከጨዋታ ውጪ ተብላ ተሽራለች፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ሀዋሳ ከተማዎች የተሻለ የተንቀሳቀሱበት፤ ንግድ ባንኮች በበኩላቸው ያስቆጠሩትን ግብ አስጠብቆ ለመውጣት በሚመሰል መልኩ ረጃጅም ኳሶችን ሲጠቀሙ የተመለከትንበት ነበር፡፡ የአጥቂ ክፍላቸውን ለማጠናከር ይረዳቸው ዘንድ ተጫዋቾችን አከታትለው ያስገቡት ሀዋሳዎች አቻ ለመሆን ዕድሎችን ከየትኛውም አቅጣጫ በሚገኙ ኳሶች ለማግኘት እጅጉን ሲጥሩ ተስተውሏል፡፡ 50ኛው ደቂቃ መሳይ ተመስገን የባንክ ተጫዋቾች አልፋ ወደ ሳጥን እየገፋች ከገባች በኃላ ለምስር ኢብራሂም ሰጥታት አጥቂዋም ወደ ጎል ስትመታ ኳሱ ኃይል ስላልነበረው በቀላሉ ንግስቲ ይዛባታለች፡፡

በቀሩት ደቂቃዎች ባንኮች የመሪነታቸውን ለማስጠበቅ ያደረጉት ጥረት ስኬታማ ሆኖላቸው ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው 1ለ0 በንግድ ባንክ አሸናፊነት ተገባዷል፡፡ ይህን ውጤት ተከትሎም ከተከታዩ መከላከያ በአራት ነጥብ ከፍ ብሎ እየመራ የሚገኘው ንግድ ባንክ በቀጣይ ሳምንት አዳማን ካሸነፈ ወይም ተከታዮቹ ከተሸነፉ የ2013 ቻምፒዮን መሆኑን ያረጋግጣል።

*በጨዋታው 82ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳ ተከላካይ ቅድስት ዘለቀ ከእመቤት አዲሱ ጋር የሜዳ የቀኝ ክፍል አካባቢ ኳስን ለማግኘት ሲሻሙ በተፈጠረ ግጭት ጉዳት ገጥሟት ወደ ሆስፒታል በአምቡላንስ አምርታለች፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም ተጫዋቿ በመልካም ጤንነት ከሆስፒታል መውጣቷን አረጋግጣለች፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ