​የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ 4-0 ማላዊ

በዋልያዎቹ አሸናፊነት ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ – ኢትዮጵያ

ስለጨዋታው

የወዳጅነት ጨዋታ ዋና ጥቅሙ የቡድንህን አቋም አሁን ያለበትን ነገር ለማየት ነው። ከዋናው ጨዋታ በፊት ይህን ነገር ማግኘታችን ጥሩ ነው። በሁለቱም አጋማሾች ቀጣዩን የነጥብ ጨዋታ ታሳቢ ያደረገ እንቅስቃሴ ለማድረግ ነው የሞከርነው። የምናስተካክላቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉ ይሰማኛል ግን ሁለቱም አጋማሽ መልካም ነው የነበረው። ስድስት ተጫዋቾች ቀይረን የተጫወትን በመሆኑ በግልፅ ቡድኑን እንደዚህ ነበረ ብሎ ለመናገር ግን ከባድ ነው። 

ስለቡድኑ አቋም

እንደቡድን ከመጀመሪያም ስጋታችን የነበረው ከዚህ በፊት እንደለመድነው የመዘጋጃ በቂ ጊዜ አለመኖሩ ነበር። ያ ራሱን የቻለ ተፅዕኖ ይኖረዋል። ያም ቢሆን ግን በተጣበበ ጊዜም ውስጥ እየሰራን የመጣነው ነገር መልካም ነው።

ቡድኑ በርካታ ግብ ስለማስቆጠሩ

በመጪው ጨዋታ ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን የተሻለ ጎል ማግባትም ይጠበቅብናል፤ ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምናስብ ከሆነ። ስለዚህ ከዛ አንፃር አሁንም ቢሆን ማረም ያለብን ነገሮች አሉ። ግን የበለጠ ጎል ማግባት መቻላችን ተጫዋቾች የበለጠ በራሳቸው ላይ ዕምነት እንዲኖራቸው ያደርጋል። ዝም ብለን ለቡድኖች የምንሰጠው የተጋነነ ግምት አለ። ከዛ ነገር ወጥተን በእንቅስቃሴ ብልጫ መውሰድ ስንጀምር የተሻለ ይሆናል። እነሱ የወዳጅነት ጨዋታም ቢሆን በጉሽሚያ ለማቆም ነበር የሚሞክሩት እዛ ነገር ላይ ትኩረት አድርገን መስራት ከቻልን እና እንቅስቃሴው ካለ ግቡም መምጣት ይችላል የሚል ግምት ነው ያለኝ።

አሰልጣኝ ሜክ ምዋኔ – ማላዊ

ስለጨዋታው

ከደቡብ ሱዳን ጋር ላለብን ጨዋታ ምን ሁኔታ ላይ እንደሆንን ለማወቅ ያደረግነው ጨዋታ ነበር። ነገር ግን የምንፈልገው ደረጃ ላይ አለመሆናችንን ተረድተናል። ያንን ጨዋታ ለማሸነፍም በጣም ጠንክረን መስራት ይኖርብናል።

ስለተጋጣሚያቸው

በጨዋታው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥሩ ነበር ፤ ከባድ ጨዋታንም ሰጥቶናል። ለደቡብ ሱዳኑ ጨዋታ በጣም መዘጋጀት ይኖርብናል።

ስለበድናቸው ብቃት

በሀገር ውስጥ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ነው የተጠቀምነው ዛሬ። ከደቡብ ሱዳኑ ጨዋታ በፊት ኢንተርናሽናል ተጫዋቾች ይቀላቀሉናል። ከዛሬዎቹ የተወሰኑት ዝግጁ ናቸው የተወሰኑት ደግሞ አይደሉም። ስለዚህ ከሚመጡት ጋር አጣምረን ይበልጥ መዘጋጀት አለብን።

© ሶከር ኢትዮጵያ