ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሀዋሳ ከተማን አሸንፏል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የአስራ ሰባተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ሦስተኛ ጨዋታ ከሰዓት ቀጥሎ የአዲስ ንጉሤ ግሩም የቅጣት ምት ጎል ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሀዋሳን 1ለ0 እንዲረታ አስችሏል፡፡

10፡00 ሲል ከዋንጫ ፉክክሩ መውጣቱን ያረጋገጠው እና ሁለተኛ ደረጃን ለመያዝ እየታገለ በሚገኘው ሀዋሳ ከተማ እና ሶስተኛ ደረጃን ለማግኘት እየጣረ ባለው ኢትዮ ኤሌክትሪክ መካከል የተደረገው ጨዋታ በኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ መሪነት ጀምሯል፡፡ ሀያ ደቂቃዎችን ያህል በእንቅስቃሴ የተዳከመው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ብዙም ትኩረት የሚስቡ ነገሮችን ባንመለከትም በሙከራ ረገድ ሀዋሳዎች በእንቅስቃሴ ደግሞ በአንፃራዊ መልኩ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ተሽለው የታዩበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ 5ኛው ደቂቃ ነፃነት መና ለመሳይ ተመስገን ከቀኝ በኩል በግል ጥረቷ ወደ ግራ በኩል አሳልፋላት አጥቂዋም ሁለት ጊዜ ገፋ በማድረግ ወደ ግብ ተጠግታ ብትመታውም የኤሌክትሪክ ተከላካዮች ተረባርበው ባወጡባት አጋጣሚ ሀዋሳዎች በሙከራ ቀዳሚ መሆን ችለዋል፡፡

18ኛው ደቂቃ በእንቅስቃሴ ደከም ቢሉም በሙከራ ረገድ የመሳይ ተመስገን ግልጋሎት በፈጣን ሽግግር ለመጠቀም የጣሩት ሀዋሳዎች ሁለተኛ ሙከራቸው አድርገዋል፡፡ ነፃነት መና ለመሳይ ሰጥታት አጥቂዋ ወደ ጎል በቀጥታ ስትመታ ትዕግስት አበራ ስትመልስባት ከተከላካዮች ጀርባ ነፃነት ሾልካ መታ ኳሱን ለማግኘት ብትሞክርም አምልጧታል፡፡

ከዚህ ሙከራ በኃላ ሁለት ደቂቃ እንደተቆጠረ መሳይ ተመስገን ሌላ ሙከራን ከቅጣት ምት ስትመታ ትዕግስት የያዘችባት ሌላኛዋ የክለቡ ሙከራ ነች፡፡

በእንቅስቃሴ ረገድ ከተጋጣሚያቸው ሻል ያሉት ኤሌክትሪኮች ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል ደርሶ ግብ ለማስቆጠር ግን ተገድበዋል፡፡ 40ኛው ደቂቃ ከቀኝ በኩል በመልሶ ማጥቃት በረጅሙ ሳራ ነብሶ ደርሷት መረጋጋት ባለመቻሏ ኳሱን ወደ ላይ የሰደደችበት ኤሌክትሪኮች ካደረጉት ላቅ ያላችዋ ነበረች፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ሀዋሳ ከተማዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በባሰ ሜዳ ላይ ተቀዛቅዘው የታዩበት ኤሌክትሪኮች ተመሳሳይ የመቀዛቀዝ ስሜት ቢንፀባረቅባቸውም ትጋት አብሯቸው መኖሩ በመጀመሪያው አጋማሽ የታየባቸውን ዕድሎችን የመፍጠር ሁነትን አሻሽለው መቅረብ የቻሉበት ነበር፡፡

መሳይ ተመስገን 50ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት አክርራ መታ ትዕግስት በያዘችባት ኳስ ሀዋሳዎች በሙከራ በዚኛው አጋማሽም ቀዳሚዎች ሆነዋል፡፡ቀስ በቀስ ወደ መስመር ባደላ እንቅስቃሴ ወደ ጨዋታ ቅኝት የገቡት ኤሌክትሪኮች እፀገነት ብዙነህ ከመስመር አሻግራ ፍሬወይኒ ገብረፃድቅ ለጥቂት መጠቀም ባልቻለችው ኳስ ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል ለመጠጋት ጥረትን አድርገዋል፡፡

በተወሰነ ረገድ ከስህተታቸው በመታረም ሙከራን ለማድረግ ሲታትሩ የታዩት ሀዋሳዎች በሚሻገሩ ኳሶች ለመጠቀም ሞክረዋል፡፡ ፀሀይነሽ ጁላ በረጅሙ ወደ ግብ የላከችውን ካሰች ፍሰሀ በግንባር ገጭታ በሚያስቆጭ ቅፅበት የወጣባት ምናልባት ሀዋሳዎች መሪ ሊሆኑ ሚችሉበት ነበር፡፡

75ኛው ደቂቃ ዮርዳኖስ ምዑዝ ለሳራ ነብሶ አቀብላ ከበረኛ ተገናኝታ ተጫዋቿ ካመከነች አስር ደቂቃዎች እንደተቆጠሩ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የማሸነፍያ ግባቸውን አግኝተዋል፡፡ 85ኛው ደቂቃ ወደ ግራ በኩል ወደ ረዳት ዳኛዋ ቦታ ከተጠጋ ቦታ የተገኘውን የቅጣት ምት ተቀይራ ወደ ሜዳ የገባችው አዲስ ንጉሤ በቀጥታ ወደ ጎል አክርራ ስትመታ የሀዋሳ ግብ ጠባቂ ገነት ኤርሚያስ ስህተት ታክሎ ኳሷ ከመረብ አርፋለች፡፡

ጨዋታው እስኪጠናቀቅ በቀሩት ደቂቃዎች ሀዋሳዎች አቻ ለመሆን ተደጋጋሚ ዕድሎችን ለመፍጠር ተግተዋል፡፡ በተለይ ከማዕዘን ምት ምስር ኢብራሂም አሻምታ መቅደስ ማሞ በግንባር ገጭታ ትዕግስት አበራ እንድምንም ያወጣቻት ምናልባት በመጨረሻም ሀዋሳን አቻ የምታደርግ ብትሆንም ወደ ጎልነት መለወጥ ሳትችል በኤሌክትሪክ 1ለ0 አሸናፊነት ጨዋታው ተደምድሟል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ