“አሁን ወደ ምፈልገው እንቅስቃሴ ገብቻለው” – ሱራፌል ዳኛቸው

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዛሬው የማላዊ የወዳጅነት ጨዋታ ተቀይሮ በመግባት ጎል ከማስቆጠሩ በተጨማሪ ጥሩ መንቀሳቀስ ከቻለው ሱራፌል ዳኛቸው ጋር ሶከር ኢትዮጵያ አጭር ቆይታ አድርጋለች።

ባለፉት ሦስት ዓመታት ካሳየው አስደናቂ አቋም አንፃር ዘንድሮ በብዙ ነገር ቢጠበቅም አጀማመሩ ቀዝቀዝ ያለ መሆኑ ጥያቄዎች ሲነሱበት ነበር። በዚህ ምክንያት በክለቡ በተደጋጋሚ ተቀይሮ መውጣት እና በተጠባባቂ ወንበር ለመቀመጥ ከመገደዱ ባሻገር ከብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውጭ ሆኖ እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። የ2011 የፕሪምየር ሊግ ኮከብ ተጫዋቹ በቅርብ ጨዋታዎች ወደ ቀደመ አቋሙ እየተመለሰ መሆኑን የሚያሳይ እንቅስቃሴ በማድረግ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ በድጋሚ መጠራት ችሏል። በዛሬው ዕለት በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከማላዊ ጋር በነበረ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ላይም ተቀይሮ በመግባት ግሩም ጎል ከማስቆጠሩ ባሻገር አቡበከር ላስቆጠረው ጎል አመቻችቶ በማቀበል መልካም እንቅስቃሴ አሳይቶ ወጥቷል።

ከጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ከዚህ ቀደም ከወቅታዊ አቋሙ ጋር በተያያዘ ለሶከር ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የሰጠውን አስተያየት እያሳካ ስለመሆኑ ጥያቄ አቅርበንለት ተከታዩን አጭር ምላሽ ሰጥቶናል።

” የሚፈለገው ሱራፌል አይደለሁም፤ በቀጣይ ትክክለኛው ሱራፌል ይመጣል ብዬ ነበር። እውነት ነው፤ አሁን መሻሻሎች አሉ። ሆኖም የሚቀሩኝ ነገሮች ስላሉ እነሱን በማስተካከል በቀጣይ ትክክለኛው ሱራፌል ሆኜ እመጣለሁ።

” በብሔራዊ ቡድን አለመጠራቴ ያነሳሳኛል እንጂ ሌላ ብዙም ነገር የለም። ‘አለመጠራቴ ጥሩ ነው’ ብዬ ነግሬህ እንደነበረም አስታውሳለው። በሚገባ አሁን ወደ ምፈልገው እንቅስቃሴ ገብቻለው። ዛሬ ለሀገሬ ጎል ማስቆጠሬ ብቻ ሳይሆን ከኳስ ጋር ያለኝ ግኑኝነት ጥሩ ነበር። ብዙ ኳስ ሳይበላሽቡኝ በደንብ ጨዋታወን ተቆጣጥሬ መጫወት ችያለሁ። ይህን እንቅስቃሴም በክለቤ እያሳየሁ ነው። ወደምፈልገው ሪትም እየመጣሁ ነው። ለራሴም የሚነግረኝ ጥሩ ስሜት ቢኖርም ገና ነኝ፤ የሚቀረኝ ነገር አለ።

” በዛሬው ጨዋታ ጥሩ መንቀሳቀሴ እና ጎል ማስቆጠሬ የበለጠ መነሳሳት ይፈጥርልኛል። ከዚህም ቀደም እንደተናገርኩት ለብሔራዊ ቡድን አለመመረጤ ጠንክሬ እንድሰራ ያደረገኛል። በህይወትህ ሁልግዜ ጥሩ ነገር ሲያጋጥምህ ብቻ መኖር ሳይሆን አንዳንዴ የሚያጋጥሙህን ውጣ ውረዶች መጋፈጥ ያስፈልጋል። ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ እንዲሆን መጠበቅ የለብህም። አንዳንዴ መንገራገጮች ሲመጡ እነርሱን የምታልፈው ጠንክረህ ስትሰራ ነው። እኔም ጋር የመጡት አንዳንድ ነገሮች ጠንክሬ እንድሰራ አድርገውኛል። ከዚህ በኃላም የተሻለ ደረጃ ለመድረስ ጠንክሬ እንድሰራ የበለጠ እተጋለሁ፤ ጠንክሬ እሰራለሁ ብዬ አስባለሁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ